የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በመሬት መንሸራተት ለተጎዱ ወገኖች 13 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ከአማራ ልማት ማህበር ጋር በመተባበር በሰሜን ጎንደር ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች 13 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የአልባሳት ድጋፍ አድርጓል።
በድጋፍ መርሀ-ግብሩ የአማራ ልማት ማህበር ምክትል ስራ አሥፈጻሚ መዝገቡ አንዷለም፤ በቀጣይ በጎ አድራጊ አካላትን በማስተባበርና በማፈላለግ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሰርካዲስ አታሌ በበኩላቸው፤ ድጋፍ ያደረጉ ድርጅቶችን በማመስገን ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
ከዚህ በፊት መንግስት ከ500 ኩንታል በላይ የምግብ እህል በዞኑ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ መደረጉን የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመላክታል፡፡