በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመኸር ወቅት 571 ሺህ ሔክታር በዘር ተሸፈነ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመኸር ወቅት ከ571 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል፡፡
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ አድማሱ አወቀ እንዳሉት÷ በክልሉ በተያዘው ዓመት 769 ሺህ ሔክታር መሬት በማረስ በዓመታዊና ቋሚ ሰብሎች ለመሸፈን እየተሰራ ነው።
በዓመቱ ከ60 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቅሰው÷ ለዚህም የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
በክልሉ በአጠቃላይ በዋና ዋና ሰብሎች ለመሸፈን ከታቀደው 394 ሺህ ሔክታር ውስጥ እስካሁን ከ356 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው በዘር መሸፈኑን ጠቅሰዋል፡፡
የሰብል በሽታዎች እና ተባይ ቁጥጥር ሥራ ላይ ከፍተኛ ክትትል እየተደረገ እንደሆነ መናገራቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡