አቶ ጌታቸው ረዳ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ አስገነዘቡ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ላይ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መሥተዳድር ጌታቸው ረዳ አስገነዘቡ፡፡
የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም እና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ግምገማ መድረክ ተካሂዷል።
አቶ ጌታቸው ረዳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በክልሉ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጉዳይ በትኩረት እየተሠራባቸው ከሚገኙ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።
መንግሥት እርሻን ለማዘመን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት የእርሻ ግብዓት አቅርቦትን በማሻሻል፣ ግብርናን በማዘመንና የተፈጥሮ ሃብትን ጥቅም ላይ በማዋል እንዲሁም በመሰል ዘርፎች ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውንም አብራርተዋል፡፡
በክልሉ ያለውን ውስን ሀብትና አቅም በመጠቀም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተሠሩ ሥራዎች የሚደነቁ መሆናቸውንም ነው ያነሱት፡፡
በየደረጃው የሚገኙ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራር አባላት ተግባር የሚለካው የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎችን በመስራት ነው ብለዋል፡፡
ሙሉ አቅማችንና ሥራችን ልማትና የመልሶ ግንባታን ማጠናከር መሆን አለበት ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
የክልሉን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በእንስሳትና ተፈጥሮ ሃብት ልማት እንዲሁም በመስኖ ልማትና እርሻን በማዘመን ረገድ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡