ፖርቹጋል ያጋጠማትን የሰደድ እሳት ለመከላከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ፖርቹጋል ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሰደድ እሳት መከሰቱን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጇን አስታውቃለች፡፡
በሳምንቱ መጀመሪያ በሰሜናዊ ፖርቹጋል በተከሰተው የሰደድ እሳት አደጋ እስካሁን የሰባት ሰዎች ህይወት ማለፉ ነው የተገለጸው፡፡
የፖርቹጋል ጠቅላይ ሚኒስትር ሉዊስ ሞንቴኔግሮ የከፋ የሰደድ እሳት አደጋ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጃቸው ተገልጿል፡፡
በሰሜናዊ ፖርቹጋል በበርካታ ስፍራ የተቀሰቀሰውን ሰደድ አሳት ለመከላክል ከ1 ሺህ በላይ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ተሰማርተዋል ተብሏል፡፡
በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው እና ንብረታቸው ለተቃጠለባቸው ዜጎች መንግስታቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ፖሊስ የእሳት አደጋውን ምክንያት እንዲያጣራም ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡
የአውሮፓ ኮፐርኒከስ የሳተላይት አገልግሎት እንዳስታወቀው÷ የእሳት አደጋው እስካሁን 15 ሺህ ሄክታር የሚደርስ ስፍራ ያካለለ ሲሆን 210 ሺህ የሚሆኑ መኖሪያ ቤቶች በአደጋው ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡