ኖርዌይ በ2025 በነዳጅ የሚሠሩ መኪኖችን መሸጥ ላቆም ነው አለች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሜን አውሮፓዊቷ ሀገር ኖርዌይ በፈረንጆቹ 2025 በነዳጅ የሚሠሩ መኪኖችን መሸጥ ያቆመች የመጀመሪያዋ ሀገር ለመሆን አቅጃለሁ አለች፡፡
ነዳጅ ለውጭ ገበያ ከሚያቀርቡ ሀገራት አንዷ የሆነችው ኖርዌይ÷ በነዳጅ ከሚሠሩ ይልቅ የኤሌክትሪክ መኪኖች ላይ ትኩረት ማድረጓን ነው ያስታወቀችው፡፡
በሀገሪቱ ከሚገኙ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን የግል መኪኖች መካከል ከ754 ሺህ የሚልቁት በኤሌክትሪክ እንደሚሠሩ መገለጹን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አሁን ላይ በሀገሪቱ ከሚሸጡ 10 መኪኖች ዘጠኙ በኤሌክትሪክ እንደሚሠሩም ነው ዘገባው ያመላከተው፡፡
የኤሌክትሪክ መኪኖችን ለማበረታታት አሽከርካሪዎች ከፓርኪንግ እና ቀረጥ ክፍያ ነፃ መደረጋቸውም ተጠቅሷል፡፡
የሀገሪቱን መዲና ኦስሎን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ከ2 ሺህ በላይ በቂ ቻርጅ ማድረጊያ መኖሩም ተጠቁሟል፡፡