Fana: At a Speed of Life!

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ሕልፈተ-ሕይወት የተሰማውን ሐዘን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ሕልፈተ-ሕይወት የተሰማውን ሐዘን ገልጿል፡፡

ምክር ቤቱ ባወጣው የሐዘን መግለጫ÷ በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ዕንቁ ምሁራን መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱ፣ ተመራማራ፣ መምህር፣ በሳል ፖለቲከኛና ብቁ አመራር ነበሩ ብሏል፡፡

ሀገራቸውን በተለያዩ መስኮች በትጋትና በሀገር ፍቅር ስሜት ማገልገላቸውንም አውስቷል፡፡

ከደርግ መንግስት መውደቅ ማግሥት በተቋቋመው የሽግግር መንግስት የተወካዮች ምክር ምክር ቤት አባል በመሆን በሀገራችን ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲሳካ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ብሏል መግለጫው፡፡

የደቡብ ሕብረት እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት ፓርቲ ሊቀ-መንበር ሆነው ባገለገሉበት ወቅትም በቀድሞ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሃዲያ ዞን የስቄ ቁጥር ሁለት ምርጫ ክልል ሕዝብን በመወከል በ2ኛውና በ3ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ከ1993 እስከ 2002 ዓ.ም) አባል በመሆን ከሕዝብ የሰጣቸውን ኃላፊነትና አደራ ተወጥተዋል ብሏል፡፡

በየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) በሀገራችን ፖለቲካ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ ያለው መግለጫው÷ በሀገራችን ሠላማዊ የፖለቲካ ባህል እንዲዳብር እና የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት እንዲጠናከር ዐሻራቸውን አስቀምጠው አልፈዋል ነው ያለው፡፡

ለሀገርና ለሕዝብ ኖረው ሙሉ ጊዜያቸውንና ጤናቸውን መስዋዕት ያደረጉ ሀገር ወዳድ ብርቱ ኢትዮጵያዊ እንደነበሩም አውስቷል፡፡

የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በበየነ ጴጥሮስ (ፕ/ር) ሕልፈተ-ሕይወት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጆች እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትን ተመኝቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.