የ2024/25 የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ዛሬ ይጀምራል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 7፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 36 የአውሮፓ ክለቦችን የሚያሳትፈው አዲሱ የአውሮፓ ሻምፒየንስ ሊግ ውድድር ዛሬ ሲጀመር ኤሲ ሚላን በሜዳው ሳንሲሮ ከሊቨርፑል የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል፡፡
በብዙዎች ያልተወደደው የሻምፒየንስ ሊጉ አዲሱ የውድድር ቅርፅ በአውሮፓ እግር ኳስ የበላይ ጠባቂዎች ይሁንታ ከአገኘ ወዲህ ዛሬ ምሽት መተግበር ይጀምራል፡፡
ውድድሩ ዛሬ ሲጀመር ምሽት 1 ሠዓት ከ45 ላይ የስዊዘርላንዱ ያንግ ቦይስ ከእንግሊዙ አስቶንቪላ እንዲሁም ጁቬንቱስ ከፒኤስቪ አይንድሆቨን ይገናኛሉ፡፡
ሌሎች የዛሬ መርሐ-ግብሮች ሲቀጥሉም÷ የፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝበን ከፈረንሳዩ ሊል፣ ሪያል ማድሪድ ከጀርመኑ ስቱትጋርት፣ ኤሲ ሚላን ከሊቨርፑል እንዲሁም ባየርን ሙኒክ ከክሮሺያው ዳይናሞ ዛግሬብ በተመሳሳይ ምሽት 4 ሠዓት ላይ ይጫወታሉ፡፡
ዘንድሮ በሚተገበረው አዲሱ የውድድር ቅርፅ መሠረት እያንዳንዱ ቡድን ሥምንት ጨዋታዎችን የሚያደርግ ይሆናል፡፡
በውድድሩ ከ 1 እስከ 8 ደረጃን ይዘው የሚያጠናቅቁ ቡድኖች በቀጥታ ሩብ ፍፃሜን እንደሚቀላቀሉ የወጣው መርሐ-ግብር ያስረዳል፡፡
ከ9 እስከ 24 ደረጃ የሚይዙት ደግሞ በደርሶ መልስ ጨዋታ አሸናፊው ቡድን ሩብ ፍፃሜውን የሚቀላቀል ይሆናል፡፡