Fana: At a Speed of Life!

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት እስካሁን 10 ሚሊየን ያህል ሰዎች መመዝገባቸው ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት እስካሁን 10 ሚሊየን ያህል ሰዎች መመዝገባቸውን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

ዓለም አቀፍ “የመታወቅ ቀን” በመስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።

ቀኑን አስመልክቶ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ፤ መታወቂያ ማግኘት የዜጎች መብት ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊ መብት ነው ብሏል።

መሠረታዊ አገልግሎትን ለማግኘት፣ መብትን ለማስጠበቅ እና በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ላይ ተሳትፎ ለማድረግ አስፈላጊ ስለሆነ፣ ሁሉም ሰው መታወቅ እንደሚገባውና ሁሉም ሰው የመታወቅ መብት እንዳለውም ጠቁሟል፡፡

በፈረንጆቹ መስከረም 16 ቀን የሚከበረው ዓለም አቀፍ “የመታወቅ ቀን” በኢትዮጵያ ዲጂታል መታወቂያን በተመለከተ መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ፣ የ“ፋይዳ” ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ አስፈላጊነት፣ የዜጎችን ተጠቃሚነትና መብቶችም መረጃ በመስጠት እየተከበረ ነው፡፡

ቀኑ ሲከበር ዜጎችን ለዲጂታል መታወቂያ በማብቃት፣ አገልግሎቶችን በማሳደግ እና በኢኮኖሚ እድገት ላይ ያለውን ሚና በማሳየት ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗ በአፍሪካ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ቀዳሚ አድርጓታል ተብሏል፡፡

የዘንድሮው ዓመት የመታወቅ ቀን ግለሰብ እና ማህበረሰብን የሚያበቃ፣ ሁሉንም አካታች የማንነት ስርዓት አስፈላጊነት አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ከመስከረም 6 እስከ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ባሉት ቀናት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም በመላው ሀገሪቱ ቁልፍ ቦታዎች ላይ ከሚደረገው የፋይዳ የዘመቻ ምዝገባ ጎን ለጎን የፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤትና የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመሆን የኦንላይን ስርጭቶች፣ የምዝገባ እንቅስቃሴዎች ጨምሮ የተለያዩ ተከታታይ ዝግጅቶችን ይከናወናሉም ነው የተባለው፡፡

የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት እስካሁን 10 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎችን እንደመዘገበም የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መረጃ ያመላክታል፡፡

የመታወቅ ቀንን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ቁልፍ ፕሮጀክት የሆነውን በፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ነዋሪዎቿ እንዲመዘገቡ የንቅናቄ ሥራዎች ይሠራሉም ተብሏል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.