የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 6፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ የግድያ ሙከራ እንደተደረገባቸው ተሰምቷል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ ፍሎሪዳ በሚገኘው የጎልፍ ክለባቸው ውስጥ በነበሩበት ወቅት ነው የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው፡፡
በወቅቱ የአሜሪካ ደህንነት መስሪያ ቤት ሴክሬት ሰርቪስ አባላት ኤኬ47 የተሰኘ የጦር መሣሪያ የታጠቀ ግለሰብ የግድያ ሙከራ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ ተመልክተው ተኩስ እንደከፈቱበት ተገልጿል፡፡
በግድያ ሙከራ የተጠረጠረው ግለሰብ በመኪና ለማምለጥ 61 ኪሎ ሜትር ካሽከረከረ በኋላ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተመላክቷል፡፡
ተጠርጣሪው ራያን ዌስሊ ራውዝ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ዩክሬንን የሚደግፉ የተለያዩ መረጃዎችን ያጋራ እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
በተለይም የውጭ ዜጎች የዩክሬንን ጦር በመቀላቀል ሩሲያን እንዲዋጉ በርካታ ሃሳቦችን ሲሰጥና ለመመልመልም ሙከራ ሲያደርግ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በድጋሚ ከተደረገባቸው የግድያ ሙከራው ተርፈው ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ ላይ እንደሚገኙ ተጠቅሷል፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ የግድያ ሙከራ ሲደረግባቸው ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡
ትራምፕ ከ2 ወራት በፊት በፔንሲልቬኒያ ግዛት የምርጫ ቅስቀሳ እያካሄዱ ባሉበት ወቅት የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው እንደነበር አልጀዚራ በዘገባው አስታውሷል፡፡