የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት ለማስቆም የሚከናወን የትኛውም እንቅስቃሴ ተገቢነት የለውም – አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት ለማስቆም የሚከናወን የትኛውም እንቅስቃሴ ተገቢነት እንደሌለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ የዘወትር መሻት ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ አግባብ የውሃ ሃብቷን ተጠቅማ ልማቷን ማረጋገጥ መሆኑን አምባሳደርታዬ አጽቀሥላሴ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ልማቷን ከማረጋገጥ ውጪ የትኛውንም ሀገር የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት ጠቁመው ፥ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም ለዚሁ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ግድቡ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
አምባሳደር ታዬ ÷ ኢትዮጵያ ያሏትን የተፈጥሮ ሃብቶች ተጠቅማ ልማቷን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራች መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ ታዳሽ ኃይልን መሰረት በማድረግ የኃይል ፍላጎቷን ለማሟላት እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው ፥ ለዚህም የውሃ ሃብቷን ለመጠቀም እያከናወነች ያለው ስራ ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መርሆችንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ መልኩ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ጽኑ አቋም እንዳላት መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
ሆኖም ግን በዓባይ ወንዝ ላይ የቀኝ ግዛት ውሎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት ከመሰረቱ ተቀባይነት እንደሌለው አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት ለማስቆም የሚከናወን የትኛውም እንቅስቃሴ ተገቢነት የሌለውና የማይሳካ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡