የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ፍትሃዊ የግብይት ሰርዓት እንዲኖር ከፍተኛ ሚና እያበረከቱ ነው – ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ፍትሃዊ የግብይት ሰርዓት እንዲኖር ከፍተኛ ሚና እያበረከቱ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
መንግስት ምክንያታዊ ያልሆነ የአቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት እንዲከሰት የሚያደርጉ ነጋዴዎች ህጋዊ መስመር እንዲይዙ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
በህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ ከሚወሰደው እርምጃ ጎን ለጎን የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች እንዲጠናከሩ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ 1 ሺህ 137 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች መደራጀታቸውን ጠቅሰው ፥ ገበያዎቹ ፍትሃዊ የግብይት ስርዓት እንዲኖር ከፍተኛ ሚና እያበረከቱ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ለበርካታ ዜጎች እንደዋና የገበያ መዳረሻ ሆነው እያገለገሉ መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡
በሌላ በኩል የምርት አቅርቦት ተደራሽነትን ለማቀላጠፍ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ይህ ተግባር በቀጣይም ተጠናክሮና እንደሚቀጥል ገልጸው ፥ ባለድርሻ አካላትም የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡