በሲድኒ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተከታትለው በመግባት አሸነፉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአውስትራሊያ ሲድኒ ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተከታትለው በመግባት አሸነፉ።
በዓለም አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ በተሰጠው በሲድኒ ማራቶን አትሌት ወርቅነሽ ኢዴሳ 2:21:40 በሆነ ሰዓት በመግባት የቦታውን ክብረ ወሰን በማሻሻል ጭምር ውድድሩን አሸንፋለች።
አትሌት ሩቲ አጋ 2:23:09 እንዲሁም አትሌት ጎይተቶም ገብረሥላሴ 2:24:16 በሆነ ሰዓት በመግባት ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ በመያዝ ውድድሩን አጠናቀዋል።
በወንዶች ደግሞ ኬኒያዊው አትሌት ብሪሚን ሚሶይ 2:06:17 በሆነ ሰዓት በመግባት ውድድሩን ሲያሸንፍ፤ ኢትዮጰያዊው አትሌት ጫሉ ደሶ 2:08:01 በመግባት ውድድሩን ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል።
በውድድሩ ብርቱ ፉክክር ሲያደርጉ የነበሩት አትሌት ልዑል ገብረስላሴ እና ታዱ አዳቴ ስድስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃን ይዘው ውድድሩን ጨርሰዋል።