Fana: At a Speed of Life!

መድረኩ አመራሩ ሀገራዊና ቀጣናዊ ሁኔታዎችን ተረድቶ ለቀጣይ ተልዕኮዎች ብቁ እንዲሆን ያስችላል – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከፍተኛ የብልጽግና አመራሮች የተሳተፉበት የአቅም ግንባታ መድረክ አመራሩን ሀገራዊ፣ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን ተረድቶ ለቀጣይ ተልዕኮዎች ብቁ ሆኖ እንዲቆም የሚያስችል ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንትና በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡

አቶ አደም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ከ2 ሺህ በላይ ከፍተኛ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች የተሳተፉበት የአቅም ግንባታ መድረክ “የህልም ጉልበት ለእምርታዊ እድገት” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአዳማ ከተማ መጀመሩን ገልጸዋል።

መድረኩ በዋናነት አመራሩን ሀገራዊ፣ቀጣናዊ እና አለምአቀፋዊ ሁኔታዎችን በሚገባ ተረድቶ ለቀጣይ ተልዕኮዎች ብቁ ሆኖ እንዲቆም የሚያስችል እንደሆነም ጠቁመዋል።

ለዚህም በስልጠናው ላይ ተግባራዊ በሚደረጉ የሰነድ ገለፃዎች፣የቡድን ውይይቶች፣የሀይል መድረኮች እና ምላሾች የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት በአመራሩ ዘንድ እንዲፈጠር ስልጠናው በር ከፋች እንደሚሆን እምነቴ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አመራሩ ከሚቀስመው እውቀት በተጨማሪም በሚኖሩ የልምድ ልውውጥና የቡድን ውይይት መድረኮች ፓርቲውን እና መንግስትን የሚያጠናክሩ ግብዓቶችን ሰልጣኞች በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያገኙ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በመጀመሪያው ቀን ውሎም በብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት የቀረበው በሕዝቦች ትስስር፣በዜጎች ክብር፣በሰብአዓዊ ብልፅግና እና በሀገራዊ ልዕልና ላይ መሰረት አድርጎ እንዲገነባ የምንፈልገው የኢትዮጵያ ህልም ላይ ሰፊ ገለፃ ቀርቦ የጋራ መግባባት የጨበጥንበት ነው ብለዋል።

በቀጣይ ቀናትም በሚቀርቡ የተለያዩ ይዘቶችን ባዘሉ ገለፃዎች የብሔራዊነት ትርክትን ለማስረጽ፣ የሪፎርም ሥራዎቻችንን ይበልጥ ውጤታ ለማድረግ፣ የማስፈፅምና የመፈፀም ብቃትን ለማሳደግ በአጠቃላይ ህልምን ለማሳካት የሚያስችሉ ሀገራዊ ቁልፎችን አመራሩ በጋራ የሚጨበጥበት እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.