Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር) ለነቢዩ መሐመድ(ሰዐወ) የልደት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) የልደት በዓል (መውሊድ) የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

እንኳን ለነቢዩ መሐመድ(ሰዐወ) የልደት በዓል (መውሊድ) በሰላም አደረሳችሁ።

የመውሊድ በዓል መጠራታችንን የምናስብበት ቀን ነው። ነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) የመጡበትን ተልዕኮ፤ የሠሩትን ሥራና ያመጡትን ውጤት እናስባለን።

ሰው ዝም ብሎ ወደ ዓለም አይመጣም። ተልዕኮ አለው። ታላላቅ ሰዎች የምንላቸው ሁሉ የመጡበትን ተልዕኮ ያወቁ፤ ዐውቀው ተልዕኳቸውን ለማሳካት የሠሩ፤ ለተልዕኳቸው ስኬትም ተገቢውን መሥዋዕትነት የከፈሉ ናቸው።

የነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) መምጣት ዓለምን በፊት ከነበረችበት መልክና ጠባይ ቀይሯታል። መምጣታቸው የዓለም ታሪክ መክፈያ ሆኗል። በዘመናቸው መሥራት ያለባቸውን ሥራም ሠርተዋል።

ለምን ወደዚህች ዓለም መጣሁ? የእኔ ተልዕኮ ምንድን ነው? ያ ተልዕኮስ የሰው ልጅን ሕይወት ወደ በጎ ምእራፍ የሚለውጥ ነው ወይ? ያንን ተልዕኮስ እያሳካሁት ነው ወይ? የሚለውን ካሰብን፣ ሀገር ብዙ ታላላቅ ሰዎችን ታተርፋለች። የሰው ልጅ ጉዞም መልካምን ጎዳና በሚሠሩ ሰዎች የተነሣ የተቃና ይሆናል።

በዚህ የመውሊድ በዓል የሕይወት ተልዕኳችንንና የተልዕኳችንን ስኬት እያስተዋልን በዓሉን እንደምናከብር ተሥፋ አደርጋለሁ። የዘንድሮው በዓል ድርብ በዓል ነው። የዛሬ ሃምሳ ዓመት መጅሊስ የተቋቋመው በመውሊድ በዓል ቀን(ረቢ አል አወል 12ኛ ቀን) ነውና።

በድጋሚ እንኳን ለነቢዩ መሐመድ (ሰዐወ) የልደት በዓል(መውሊድ) እና ለመጅሊስ ሃምሳኛ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

መስከረም 4፣ 2017 ዓ.ም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.