Fana: At a Speed of Life!

በኮንጎ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አሜሪካውያንን ጨምሮ 37 ግለሰቦች የሞት ቅጣት ተፈረደባቸው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወታደራዊ ፍ/ቤት በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተከሰሱ 3 አሜሪካውያን ዜጎችን ጨምሮ 37 ግለሰቦች በሞት እንዲቀጡ ወሰነ፡፡

በሞት እንዲቀጡ ከተወሰነባቸው 37 ግለሰቦች መካከል አብዘኞቹ የኮንጎ ዜጎች ሲሆን÷3 አሜሪካውያን፣ እንግሊዛዊ፣ ቤልጂዬማዊና ካናዳዊ ዜጎች እንደሚገኙበት ተመላክቷል፡፡

ፍ/ቤቱ ተከሳሾች ባለፈው ግንቦት ወር የሀገሪቱን ፕሬዚዳንት ከሥልጣን ለማስወገድ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በመፈፀም ጥፋተኛ መባላቸውን በቴሌቪዥን ባስተላለፈው የፍርድ ሒደት አስታውቋል፡፡

የፍርድ ሒደቱ ከኪንሻሳ ከተማ ዳርቻ ከሚገኘው የንዶላ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ መካሄዱን አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።

ትውልደ ኮንጎያዊ ሆኖ አሜሪካዊ ዜግነት ባለው ክሪስቲያን ማላንጋ መሪነት ተሞክሮ በከሸፈው መፈንቅለ መንግስት ሙከራ 6 ሰዎች መገደላቸው ተጠቁሟል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቴው ሚለር÷ሒደቱን እየተከታተሉት እንደሚገኙና አዳዲስ ሁነቶችን መከታተላቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.