የኢትዮጵያና ቻይና አምራች ኢንዱስትሪዎች ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ እዲዘጋጅ ስምምነት ላይ ተደረሰ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ከኢትዮጵያ እና ቻይና የተወጣጡና አቅም ያላቸው የአምራች ኢንዱስትሪ ማኅበረሰቦች ልምድ የሚለዋወጡበት መድረክ ለማዘጋጀት ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡
በኢትዮጵያ እና ቻይና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴሮች መካከል የሀገራቱን ንግድና ኢንቨስትመንት ለማጠናከር ያለመ ምክክር ተደርጓል፡፡
በውይይቱ ላይም ከሁለቱ ሀገራት የተወጣጡና አቅም ያላቸው የአምራች ኢንዱስትሪ ማኅበረሰቦች የልምድ ልውውጥ የሚያድረጉበት መድረክ እዲዘጋጅ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የልምድ ልውውጡ የቻይና አምራች ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አቅም፣ ምቹ የፖሊሲና የኢንቨስትመንት አማራጭን ተረድተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ይረዳል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ አምራች ባለሃብቶችም ከቻይና ባለሃብቶች ጋር በጥምረት ኢንቨስት በማድረግ ትስስራቸውን በይበልጥ እንዲያጠናክሩ ያግዛል መባሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡