Fana: At a Speed of Life!

የሻይ ቅጠል ማሳ ሽፋንን ከአምስት ዓመታት በኋላ 500 ሺህ ሄክታር ለማድረስ እየሰራን ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የሻይ ቅጠል ማሳ ሽፋንን ከአምስት ዓመታት በኋላ 500 ሺህ ሄክታር ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው የሻይ ቅጠል ኢኒሼቲቭን በተመለከተ ባወጡት መረጃ፤ ክልሉ በግብርናው ዘርፍ ለማሳካት እየሠራባቸው ካሉ ግቦች አንዱ የወጪ ምርቶችን መጠን ማሳደግ፣ ብዝሃነት መጨመር እና ጥራት ማሻሻል ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል።

ይህን ግብ በማሳካት ረገድ የሻይ ቅጠል ኢኒሼቲቭ ልማት ድርሻ ከፍተኛ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

የሻይ ቅጠል ልማት በአንድ ወረዳ ውስጥ በአንድ የግል ድርጅት ብቻ ተወስኖ እንደነበር አስታውሰው፤ በ2013 ዓ.ም ወደ ስራ ባስገባነው “የአሌይ አዋጅ” በመቀየር፣ በአሁኑ ጊዜ በምዕራብ ኦሮሚያ አራት ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ውስጥ ማስፋፋት ችለናል ሲሉ ገልጸዋል።

በ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመን ሽፋናችንን በበርካታ እጥፍ ለማሳደግ አቅደን ስንንቀሳቀስ የነበረ ሲሆን፣ ከተዘጋጁ የሻይ ችግኞች ውስጥ ለተከላ የደረሱትን ሙሉ በሙሉ ማልማት ችለናል ብለዋል።

ክልሉ በዘርፉ ያለው እምቅ አቅም ሰፊ በመሆኑ እስካሁን የተመዘገበው መልካም እድገት ጅማሮ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚሁ መሠረት ከክልላችን የአየር ንብረት ብዝሃነት ጋር የሚስማሙ የሻይ ችግኝ ዝርያዎችን በስፋት በማዘጋጀት ሽፋናችንን ቀስ በቀስ በመጨመር ከአምስት ዓመታት በኋላ 500 ሺህ ሄክታር ለማድረስ አቅደን በመስራት ላይ እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ወጣቶችንና አርሶ አደሮችን ከሻይ ቅጠል ልማት ጎን ለጎን፣ የወጪ ንግድ ደረጃን ወደሚያሟላ ሰፊ የሻይ ቅጠል “አግሮ ፕሮሰሲንግ” በቀጥታ እንዲገቡ ለማስቻል፣ የሙያ ክህሎት፣ የስራ ፈጠራ እና የኢንቨስትመንት የስልጠና ፓኬጆች በማዘጋጀት እንዲሁም የፋይናንስ አቅርቦት በማመቻቸት ጅማሮውን ወደ ቀጣዩ እርከን በማሸጋገር ላይ እንገኛለን ብለዋል።

እስካሁን የታየው በየደረጃው ያለ አመራር ቁርጠኝነት፣ የግብርና ባለሙያዎች ጥንካሬ፣ የአርሶ አደሩ ተሳትፎና የወጣቱ አሳታፊነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስት የሂደቱን ግለት ለመጠበቅ በሁሉም ረገድ የማያቋርጥ ክትትልና ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.