ዲጂታል መታወቂያ ደህንነቱ የተጠበቀ መንግስታዊ አገልግሎት ለመዘርጋት እንደሚያስችል ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ዲጂታል መታወቂያ አካታችና ደህንነቱ የተጠበቀ መንግስታዊ አገልግሎት ለመዘርጋት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም “የመታወቅ መብት” በሚል መሪ ሃሳብ መስከረም 6 ቀን 2017 ዓ.ም የሚከበረውን የመታወቂያ ቀን አስመልክቶ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎችን ያሳተፈ የበይነ መረብ ውይይት (ዌቢናር) ተካሂዷል።
በብሔራዊ የመታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ ዘሚካኤል መሪነት በተካሄደው በዚህ ውይይት ዲጂታል መታወቂያ አካታችና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመዘርጋት እንደሚያስችል ተገልጿል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አማካሪ ዶክተር አብዮት ባዩ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የዲጂታል ስትራቴጂ ቀርጻ ገቢራዊ እያደረገችና በርካታ መንግስታዊ አገልግሎቶች በዲጂታል መንገድ እየተሰጡ ነው።
ሁሉም ተቋማት የራሳችውን ዲጂታል አገልግሎት እየዘረጉ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዲጂታል መታወቂያ በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማስወገድ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ለአብነትም በመንግስት ተቋማትና በተገልጋዮች መካከል የተሻለና የተፋጠነ አገልግሎት እንዲሳለጥና በቀላሉ መረጃ ለመለዋወጥ ያግዛል ብለዋል።
ይህም በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማስወገድ ለዜጎችን አገልግሎትን በቀላሉ ተደራሽ በማድረግ የአካታችነት ስርዓት እንዲፈጠር ከማድረጉም ባሻገርም ፈጠራን ለማጎልበትም ያግዛል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የአይዲፎር አፍሪካ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ዮሴፍ አቲክ ዲጂታል መታወቂያ ሰው ተኮር ፕሮግራሞች ተደራሽ በማድረግ የተገልጋየችን እርካታ ለመጨመር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በዲጂታል አስተዳደርና አገልግሎት ፖሊሲዎች አውጥታ ገቢራዊ ማድረጓን አድንቀው፤ ፋይዳ በመንግስትና በዜጎች ብሎም በባለድርሻ አካላት መካከል የመተማመን ምህዳር ያሰፋል ብለዋል።
በዓለም ባንክ የመታወቂያ ለልማት ወይም ‘አይ ዲ ፎር ዲ’ ከፍተኛ ኢኮኖሚስት ጁሊያ ክላርክ በበኩላቸው ዲጂታል መታወቂያ አካታችና ደህንነቱ የተጠበቀ አገልግሎት ለመዘርጋት ያግዛል ነው ያሉት።
በተለይ ሴቶችን ጨምሮ ከተለያዩ አገልግሎቶች ተገልለው የቆዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በቀላሉ አገልግሎት እንዲያገኙ ያግዛል።