የይዞታ ካርታ እናሰጣለን በማለት ከ29 ሚሊየን ብር በላይ ከግለሰቦች ወስደዋል የተባሉት በሙስና ወንጀል ተከሰሱ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የይዞታ ካርታ እናሰጣለን ብለው በማታለል ከ29 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ከግለሰቦች ወስደዋል የተባሉት በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰሱ።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በልደታ ክ/ከ የመሰረተ ልማትና ግንባታ ቁጥጥር ፅ/ቤት ኃላፊ የነበረው ዲነራስ ዱፌራ እና በግል ስራ የሚተዳደረው ሞቲ ዋቅቶላ የተለያዩ ግለሰቦችን ‘የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እናሰጣችኋለን’ በማለት በማታለል ከ29 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ አሳጥተዋል በማለት ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸዋል።
በአንደኛው ክስ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 ንዑስ ቁጥር (1) (ሀ) እና አንቀጽ 33፤ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 32 (1) እና (2) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
በዚህም 1ኛ ተከሳሽ በልደታ ክ/ከ የመሰረተ ልማትና ግንባታ ቁጥጥር ፅ/ቤት ኃላፊ ሆኖ ሲሰራ እንዲሁም ከህዳር 26 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የመሬት እና የመሬት ነክ ጉዳዮች አጣሪ ኮሚቴ አባል ሆኖ እንዲሰራ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልደታ ክ/ከ አስተዳደር ጽ/ቤት የተመደበ መሆኑን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በግል ስራ ከሚተዳደረውና በሙስና ወንጀል ልዩ ተካፋይ ከሆነው 2ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር 2ኛ ተከሳሽ በመስከረም ወር 2016 ዓ.ም በለሚ ኩራ ክ/ከ ወረዳ 10 ክልል ልዩ ቦታው መሪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሌሊሴ ከፍያለው ከተባለችው 3ኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር የንግድ ቤት በመሄድ የይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት (ካርታ) ለማሰራት የሚፈልጉ ሰዎች ካሉ እንድታገናኘው መጠየቁ በክሱ ተመላክቷል።
በዚህም መሰረት ግለሰቧም ለ14 አርሶ አደሮችን ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር እንዲገናኙ ያደረገች ሲሆን፤ 2ኛ ተከሳሽም ህጋዊ ሂደቱን ተከትሎ ካርታ እንደሚያሰራላቸው እና “ስራው የሚሰራው ከንቲባ ፅ/ቤት ውስጥ በሚሰራ ዲነራስ ዱፌራ በተባለ ግለሰብ ነው” በማለት የግል ተበዳዮችን ከ1ኛ ተከሳሽ ጋር እንዲተዋወቁ ማድረጉ በክሱ ተጠቅሷል።
በዚህ መልኩ በአርሶ አደሮቹ ስም በለሚ ኩራ ክ/ከ መሬት ልማትና አስተዳደር ፅ/ቤት መዝገብ ቤት ውስጥ የተደራጀ የይዞታ ማህደር መኖሩን የሚያሳይ ፎቶ ግራፍ በሞባይሉ ላይ ጭኖ ለግል ለተበዳዮች በማሳየት ሃሰተኛ መረጃ በመስጠት፣ በተጨማሪም 1ኛ ተከሳሽም ለሚ ኩራ ክ/ከ መሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት ሃላፊዎችን እና ከንቲባ ጽ/ቤት ያሉ ባለሙያዎችን በማሳተፍ እንደሚሰራ በመግለጽ እና “ስራው እያለቀ ነው ትንሽ ጠብቁ” በሚል የማዘናጊያ ቃላት በመጠቀም በማታለል እንዲያምኗቸው ካደረጉ በኋላ 2ኛ ተከሳሽ ለአርሶ አደሮቹ የተዘጋጁ በርካታ ካርታዎችን ለማሳያ የሊዝ ባለይዞታ ስም ቦንቱ ጋሩማ፣ ፉአድ ናስር፣ መስፍን ግርማ፣ ጋሮማ ምናሌ፣ ታደለች ሉኡልሰገድ፣ የተሰጠ የሚሉ ሃሰተኛ ካርታዎችን ለተበዳዮች ሰጥተው እንደነበር በክሱ ተመላክቷል።
በተለይም ጉዳዩን ለማስፈፀም በሚል ከተበዳዮች የባንክ ሂሳብ በቀጥታ እና ተበዳዮች ገቢ እዲያደርጉላቸው በመጠየቅ ግለሰቦች በ2ኛ ተከሳሽ እና በሌሎች ለጊዜው ባልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ስም በተከፈቱ የባንክ አካውንቶች ውስጥ ገቢ እንዲሆን ያደረጉ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ ጠቅሷል።
በተለይም 1ኛ ተከሳሽ በቁጥጥር ሲውል በመኖሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ ተከሳሽ የሚገለገልበት ተሸከርካሪ ውስጥ በተደረገ ብርበራ የተከሳሽ የነዋሪነት መታወቂያ እና በሴሪ ቁጥር 0690621፤ በሊዝ ባለይዞታ ስም ትግስት ለማ፣ ወርቁ ሀተው፣ ግርማ ከበደ የሚሉ ሃሰተኛ የይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እና በሃሰት የተደራጁ ማህደሮች የተገኙ መሆኑ በዐቃቤ ሕግ ተገልጿል።
በአጠቃላይ ተከሳሾች አሳሳች ነገሮችን በመናገር የግል ተበዳዮችን የንብረት ጥቅም የሚጎዳ ተግባር በመፈፀም ከተበዳዮ ላይ 29 ሚሊየን 580 ሺህ ብር በመውሰድ ጉዳት እንዲደርስ በማድረግ 1ኛ ተከሳሽ በዋና ወንጀል አድራጊነት፤ 2ኛ ተከሳሽ በልዩ ወንጀል ተካፋይነት በመሆን በመላ ሃሳባቸው እና አድራጎታቸው በወንጀሉ ድርጊት እና በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን በከባድ ማታለል የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በሁለተኛው ክስ ደግሞ ተከሳሾቹ በህገወጥ መንገድ ያገኙትን ገንዘብ ምንጩን በመደበቅ እና ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ ወደ ሌሎች ያልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ስም ወደ ተከፈቱ የተለያዩ የባንክ ሂሳቦች ውስጥ ያስተላለፉ መሆኑን ተጠቅሶ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ተከሳሾቹ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን በክሱ ላይ መቃወሚያ ካላቸው በመደበኛው ችሎት ለመጠባበቅ ለጥቅምት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጥሯል።
ተከሳሾቹ ወንጀሉ ከተፈጸመ በኋላ ተሰውረው የነበረ ቢሆንም በፀጥታ አካላት ክትትል በቁጥጥር ስር ውለው የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ሲከናወንባቸው እንደነበር ይታወሳል።
በታሪክ አዱኛ