በሶማሌና በአፋር ክልሎች መካከል ተከስቶ የነበረው ግጭት እንዲቆም መደረጉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌና በአፋር ክልሎች መካከል ተከስቶ የነበረው ግጭት እንዲቆም መደረጉን ችግሩን ለመፍታት የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
ብሔራዊ ኮሚቴው ባደረገው ግምገማ የመጀመሪያው ምዕራፍ አፈጻፀም ውጤታማ በመሆኑ ወደሁለተኛው የትግበራ ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚያስችለውን ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዱዓለምና የሁለቱ ክልሎች ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም የፌደራልና የክልል የፀጥታና ደኅንነት አካላት በተገኙበት የኮሚቴው የመጀምሪያ ምዕራፍ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የተደረገበት መሆኑን ብሔራዊ ኮሚቴው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የላከው መረጃ ያመለክታል፡፡
በድንበር ይገባኛል ምክንያት በሶማሌና በአፋር ክልሎች መካከል ተከስቶ የነበረው አለመግባባት ወደ ግጭት አምርቶ ለብዙ ዜጎች የህይወት ህልፈትና ስደት እንዲሁም ለበርካታ ሀብትና ንብረት ውድመት ምክንያት መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻልም ከሁለቱ ክልሎችና ከፌደራል መንግስት የፀጥታና ደኅንነት አካላት የተውጣጣ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱን በቴክኒክ ኮሚቴው የቀረበው ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡
ብሔራዊ ኮሚቴው በመጀመሪያው ምዕራፍ የአፈፃፀም ሂደት ውስጥ በቀጣናው የነበረውን ግጭት የማስቆም፣ የሰዎችን ሞት የመከላከል፣ በግጭት አካባቢዎች ነፃ ቀጣና እንዲኖርና ነፃ ቀጣናው በመከላከያና በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሆኖ እንዲቆይ የማድረግ ቁልፍ አላማዎችን ይዞ ተንቀሳቅሷል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጦፌ መሐመድ እንዳሉት በብሔራዊ ኮሚቴውና በሁለቱ ክልሎች መንግስታት በኩል የተጀመረው የሰላም ጥረት በአካባቢው ተቀስቅሶ የነበረው ግጭት እንዲቆም አድርጓል፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ይቻል ዘንድ በሁለቱ ክልሎች አመራሮች መካከል በመተማመንና በወንድማማችነት ስሜት ችግሮችን ለመፍታት እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አርባ በበኩላቸው ኮሚቴውን የሚመሩ የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች፣ የአቢይና የቴክኒክ ኮሚቴው አባላትና በሁለቱ ክልሎች ውስጥ ለሚገኙ አመራሮችና ለሰላም ወዳዱ የአፋርና የሶማሌ ህዝብ በአካባቢው የነበረው ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ ላበረከቱት የጎላ አስተዋፅኦ ያላቸውን አክብሮት ገልፀዋል፡፡
በሁለቱም ክልሎች በኩል የሚስተዋሉ አፍራሽ አመለካከቶችን እየታገሉና እያረሙ መሄድ የየክልሎቹ ከፍተኛ አመራሮች ድርሻ መሆኑን ያወሱት ፕሬዝዳንቱ በመጀመሪያው ምዕራፍ የአፈፃፀም ሂደት ውስጥ የታየው ውጤት አበረታች ነው ብለዋል፡፡
በሁለቱም ክልሎች በኩል የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በቅንነት እያረሙ መሄድና የተጀመረው በመተማመን ላይ የተመሰረተ የመፍትሔ አቅጣጫ ዳር እንዲደርስ መረባረብ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡
የሰላም ሚንስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም በበኩላቸው ብሔራዊ ኮሚቴው ሲቋቋም ያነገባቸው ግጭትን የማስቆም፣ የሰዎችን ሞት የመከላከል፣ ነፃ ቀጣናን የመፍጠርና በነፃ አካባቢዎች የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች እንዲሰፍሩ የማድረግ ቁልፍ ተልዕኮዎች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ተፈፃሚ ሆነዋል፡፡
ይህም የአካባቢው ህዝብ የሰላም አየር እንዲተነፍስና እፎይታ እንዲያገኝ ያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሁለቱ ክልሎች አመራሮችና የፀጥታ ኃይሎች በኩል የሚስተዋሉ ጥቃቅን ክፍተቶች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ ብናልፍ ነፃ ቀጣናውን ለቀው ያልወጡ ታጣቂ ኃይሎች በአስቸኳይ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማድረግና ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስ በአወዛጋቢ ቀጣናዎች ውስጥ ሰፈራዎችን ከማድረግ መቆጠብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
የመጀመሪያው ምዕራፍ አፈፃጸም ስኬት ወደሁለተኛው ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚያስችል ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው በአካባቢው የተገኘው አንጻራዊ ሰላም በሁለቱ ክልሎች አመራሮች ጥረትና የሰላም ፍላጎት የተገኘ በመሆኑ ጅምሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኝ ክፍተቶችን እየደፈኑ፣ ሥጋቶችን እያረሙና በህዝቦች መካከል ያለውን የወንድማማችነት ስሜት እያጠናከሩ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ በሁለቱም ክልሎች እጅ የሚገኙ ምርኮኞችን መለዋወጥ፣ሂደቱን በሚያደናቅፉ አካላት ላይ እርምጃ መውሰድ፣ በውይይትና መግባባት ችግሮችን እየፈቱ መሄድ፣ የሰላም ስምምነቱን ሊያደናቅፉ ከሚችሉ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች መቆጠብና ችግሮችን በፍጥነት እየፈቱ ለመሄድ መረባረብ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም አቢይ ኮሚቴው በመጀመሪያው ምዕራፍ የተንጠባጠቡ ተግባራት በቶሎ እንዲፈፀሙ፤ የሁለተኛው ምዕራፍ ትግበራም እንዲጀመር በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡ ሰብዓዊ ድጋፎችን አጠናክሮ መቀጠል፤ ተፈናቃዮችን ወደቦታቸው መመለስ፣ የፖለቲካ ውይይቶችንና የህዝብ ለህዝብ መድረኮችን መፍጠር እንዲሁም በእርቅ ችግሩን እየቋጩ መሄድ ኮሚቴው በሁለተኛው ምዕራፍ ትኩረት ከሚሰጥባቸው ቁልፍ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን መረጃው አመልክቷል፡፡