የተቀናጀ የማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ድረ ገጽ ላይ መሰረቱን ያደረገ የተቀናጀ ብሔራዊ የማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት ስምምነት ተፈርሟል፡፡
ስምምነቱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ከግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደርና ከመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ጋር ነው የተፈራረመው፡፡
ስምምነቱ ድረገጽ ላይ መሰረቱን ያደረግ የተቀናጀ ብሔራዊ የማህበራዊ ዋስትና አስተዳደር ሥርዓትን ለመዘርጋት የሚያስችል ሲሆን÷ ፕሮጀክቱ በውስጡ ሰባት ንዑስ ሲስተሞች እንደያዘ ተገልጿል፡፡
የጡረታ ምዝገባን፣ የጡረታ መዋጮ ክፍያን፣ የጡረታ ተጠቃሚነትንና ሌሎች ሥርዓቶችን በማቀናጀትና በቴክኖሎጂ በማዘመን ሥራን እንደሚያቀላጥፍም ተጠቁሟል፡፡
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የጡረተኞች ክፍያን የማሰባሰብና ገቢን የማሳደግ ሥራውን በተሻለ ማዘመን የሚያስችል ጥልቅ የአሠራር ለውጥ እንደሚያመጣ መገለጹን የኢመደአ መረጃ ያመላክታል፡፡