Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ አየር መንገድን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል በተባሉ ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል በተባሉ ስድስት ግለሰቦች ላይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት ክስ ተመሰረተ።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በነ ዮሃንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል) መዝገብ በስድስት ተከሳሾች ላይ አውሮፕላንን ያለአግባብ መያዝ ወንጀል፣ የመንግስት ሰራተኛ የስራ ግዴታውን እንዳይፈጽም መቃወምና አለመታዘዝ ወንጀል ክስ በተጨማሪም በ1ኛ ተከሳሽ ብቻ ደግሞ የአየር መንገዱን መልካም ስም ለማጉደፍ ተንቀሳቃሽ ምስል በኮምፒውተር ስርዓት አማካኝነት ማሰራጨት ወንጀል የሚል ክስ አቅርቧል።

ተከሳሾቹ ዮሃንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል)፣ አማኑኤል መውጫ፣ ናትናኤል ወንድወሰን፣ ኤልያስ ድሪባ፣ ይዲድያ ነጻነት እና እሌኒ ክንፈ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው በ1ኛ ክስ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን ይኸውም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (ንዑስ ቁጥር 1/ሀ)፤ አንቀጽ 35 እንዲሁም አንቀጽ 507 ንዑስ ቁጥር 1 ሥር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።

በዚህም ተከሳሾች በሕገወጥ መንገድ በአገልግሎት ላይ ያለ አውሮፕላንን ለመያዝ አስበው በነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 3፡30 ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ግቢ ውስጥ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነውን ቦምባርዲየር ኪው 400 የሆነ የመንገደኞች ማመላለሻ አውሮፕላን በበረራ ቁጥሩ At190 ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ መቐለ ከተማ ለመጓዝ ተሳፍረው አውሮፕላኑ ለበረራ ዝግጁ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ክፍል ለአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ መቐለ ያለው የአየር ሁኔታ ለበረራ አዳጋች እንደሆነና አውሮፕላን ለማሳረፍ ስለማያስችል መብረር እንደሌለበት በደረሰው መረጃ መነሻነት በረራው ቢደረግ በሰው ሀይወት እና በንብረት ላይ የሚያደርሰውን ከባድ አደጋ ለመከላከል ጉዞው ተሰርዞ መንገደኞች ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ ሲነገራቸው በረራው በግድ መደረግ አለበት፤ አውሮፕላኑ ይከስከስ፤ አንወርድም በማለት ቀሪ ተሳፋሪዎችም እንዳይወርዱ በመክልከል አሳድመዋል በሚል በክስ ዝርዝሩ ተካቷል።

በዚህ መልኩ ከደሀንነት ቅድመ ጥንቃቄ አንጻር አውሮፕላን ለማስነሳት እና ለማሳረፍ ብቻ የተፈቀደ ቦታ ላይ ቪዲዮ በመቅረጽና በተለይም 1ኛ ተከሳሽ ቲክቶክ በተባለ ማህበራዊ ሚዲያ ሁነቱን በቀጥታ ስርጭት በማስተላለፍ ከሁለት ሰዓታት በላይ አውሮፕላኑን ተቆጣጥረው እንዳይንቀሳቀስ በማገድ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት አውሮፕላንን ያለአግባብ መያዝ ወንጀል ተከሰዋል፡፡

2ኛ ክስ በተመሳሳይ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1)(ሀ) እና አንቀጽ 440 (1) (ሀ) ሥር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ ተከሳሾች የመንግስት ሰራተኞች የስራ ግዴታቸውን እንዳይፈጽሙ ለመቃወም በማሰብ በነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 3፡30 ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ መቐለ ከተማ ለመጓዝ ተሳፍረው አውሮፕላኑ ለበረራ ዝግጁ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ክፍል ለአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ መቐለ ያለው የአየር ሁኔታ ለበረራ አዳጋች እንደሆነና አውሮፕላን ለማሳረፍ ስለማያስችል መብረር እንደሌለበት በደረሰው መረጃ መነሻነት በረራው ቢደረግ በሰው ህይወት እና በንብረት ላይ የሚያደርሰውን ከባድ አደጋ ለመከላከል ጉዞው ተሰርዞ መንገደኞች ከአውሮፕላኑ እንዲወርዱ ሲነገራቸው ፈቃደኛ አለመሆናቸው ተጠቅሷል።

በተለይም የአውሮፕላን ደህንነትን ከህገወጥ ጣልቃ ገብነት መከላከል እና መጠበቅ የስራ ግዴታ ያለባቸው የአየር መንገዱ ሰራተኞች እንዲሁም የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት የበረራ ደህንነት ባለሙያዎች የተከሳሾቹ ተግባር ለአውሮፕላኑ እንዲሁም ለተሳፋሪዎች ደህንነት አስጊ ስለሆነ እንዲወርዱ ሲጠየቁ ያለበቂ ምክንያት ለመተባበር ፈቃደኛ ሳይሆኑ አንወርድም፤ ይከስከስ በማለት ከሁለት ሰዓታት በላይ ከአውሮፕላኑ ሳይወርዱ የቆዩ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የመንግስት ሰራተኛ የስራ ግዴታውን እንዳይፈጽም መቃወምና አለመታዘዝ ወንጀል ተከሰዋል የሚል ነው።

በ3ኛ ክስ ደግሞ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን ይኸውም የኮምፒዩተር ወንጀል ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 958/2008 አንቀጽ 13 ንዑስ ቁጥር 3 ሥር የተመለከተውን ድንጋጌ መተላለፍ የሚል ክስ ቀርቦበታል።

በዚህም ተከሳሹ ከሀገሪቱ ቁልፍ መሰረተ ልማቶች አንዱ የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድን መልካም ስም እና ዝና ለማጉደፍ በማሰብ በነሐሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 3፡30 ሰዓት በሚሆንበት ጊዜ ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ መቐለ ከተማ ለመጓዝ ተሳፍሮ አውሮፕላኑ ለበረራ ዝግጁ ቢሆንም በወቅቱ የነበረው የአየር ሁኔታ ለበረራ አዳጋች በመሆኑ በረራው ተሰርዞ እንዲወርድ ሲጠየቅ ፈቃደኛ ባለመሆንና ሌላውንም ተሳፋሪ በማነሳሳት፤ ከሁለት ሰዓታት በላይ ተንቀሳቃሽ ምስል በመቅረጽ ቲክቶክ በተባለ ማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት በቀጥታ ለሀዝብ ማስተላለፍ የሚል ክስ በዝርዝሩ ይገኛል።

በዚህም በቲክቶክ ስሙ ዮኒ ማኛ በመባል የሚጠራውን ግለሰብ በቀጥታ ስርጭት እንዲገባ በመጋበዝ፤ ይሄው ግለሰብም አየር መንገዱ ደንበኞችን ለማጉላላት ያደረገው ነው፤ ጉዱን በአደባባይ እናወጣዋለን በማለት ከተከሳሽ ጋር ሆኖ በቀጥታ ስርጭት የአየር መንገዱን ስም የሚያጎድፍ መልእክት እንዲያስተላልፍ ማድረጉ ተጠቅሶ፤ በአጠቃላይ አየር መንገዱ የሰውን ሕይወት ለመጠበቅና አደጋ ለመከላከል የሰረዘውን በረራ በአየር ሁኔታ ምክንያት እንዳልተሰረዘ፤ በተቃራኒው መንገደኞችን ለማጉላላት የፈጠረው ሰበብ እንደሆነና በሰራተኞቹ አማካኝነትም እንደታገተ በማስመሰል በቀጥታ በማስተላለፍ በፈጸመው መልካም ስም ለሚያጎድፍ ተንቀሳቃሽ ምስል በኮምፒውተር ስርዓት አማካኝነት ማሰራጨት ወንጀል ክስ ቀርቦበታል።

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን ማንነት በማረጋገጥና የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው በማድረግ ክሱን በንባብ በችሎት አሰምቷል።

ክስ ከተነበበ በኋላ የተከሳሾች የዋስትና መብታቸው እንዲፈቀድ ጠበቆች የጠየቁ ሲሆን፤ ዐቃቤ ሕግ ዋስትና ሊያስከለክሉ የሚችሉ የሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ ቁጥሮችን ጠቅሶ የዋስትና መብታቸው እንዲታለፍ ጠይቋል።

የግራ ቀኙን የዋስትና ክርክር የተመለከተው ተረኛ ችሎቱ መርምሮ ብይን ለመስጠት ለመስከረም 7 ቀን 2017 ዓ.ም ቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.