Fana: At a Speed of Life!

በሲዳማ ክልል በህገ-ወጥ ሰነድ ዝግጅት፣ በገንዘብና አደንዛዥ ዕጽ ዝውውር የተጠረጠሩ በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል የተለያዩ ህገ-ወጥ ሰነዶችን በማዘጋጀት፣ በገንዘብና አደንዛዥ ዕጽ ዝውውር የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በሰጡት መግለጫ፤ የክልሉ ሰላማዊ ሂደትን ለማወክ የሚሞክሩ ግለሰቦችን ለመቆጣጠር ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተደረገው እንቅስቃሴ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል።

በዚህም ከጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉ ጸጥታ መዋቅር ባደረገው ልዩ ኦፕሬሽን በዩኒቨርሲቲዎች ስም የተዘጋጁ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች፣ ሀሰተኛ ቼኮች፣ የካርታ ፕላን፣ የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችና የተለያዩ ከተሞች ማህተሞች ከሚሰሩባቸው መሳሪዎች ጋር መያዛቸውን አስረድተዋል።

ተጠርጣሪዎቹ ተናበው ወንጀሉን ሲፈጽሙ ነበረ ያሉት አቶ አለማየሁ፤ ድርጊቶቹ ፍትህን በማዛባትና የመንግስት አገልግሎት አመኔታ እንዲያጣ በማድረግ ማህበረሰብን ለችግር የሚያጋልጡ መሆናቸውን አብራርተዋል።

እንዲሁም የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3-02712 በሆነ አይሱዙ ተሽከርካሪ ሲጓጓዝ የነበረ 18 ኩንታል አደንዛዥ ዕጽ ሎካ አባያ ወረዳ ውስጥ ከነተጠርጣሪው ጋር በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.