ሩሲያ ስድስት የብሪታኒያ ዲፕሎማቶችን ዕውቅና ሰረዘች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በስለላ ወንጀል የጠረጠረቻቸውን ስድስት የብሪታኒያ ዲፕሎማቶችን ዕውቅና መሰረዟን አስታውቃለች፡፡
የሩሲያ የፀጥታ እና ደህንነት አገልግሎት ኤፍ ኤስ ቢ÷ ዲፕሎማቶቹ የሩሲያን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ዲፕሎማቶቹ በምስራቅ አውሮፓ እና በመካከለኛው እስያ ያለውን የፖለቲካ እና ወታደራዊ ሁኔታ እንዲያስተባብሩ እንዲሁም እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሩሲያ እንድትሸነፍ ስትራቴጂካዊ እቅድ እንዲያወጡ ሃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር ብሏል፡፡
በዚህም የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስድስቱ የብሪታኒያ ዲፕሎማቶች እውቅና በመሰረዝ ከሀገሪቱ እንዲወጡ መወሰኑ ተገልጿል።
ብሪታኒያ በጉዳዩ ላይ ያለችው ነገር አለመኖሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የሩሲያ ውሳኔ ብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር ከፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጋር በተገናኙበት እና ዩክሬን የምዕራባውያንን የጦር መሳሪያዎች ልትጠቀም በምትችልባቸው ጉዳዮች ላይ ለመምከር በተዘጋጀችበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡
የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ÷ዩክሬን በረጅም ርቀት ሚሳኤሎች በሩሲያ ግዛቶች ላይ ጥቃት እንድትፈፅም የሚፈቅዱ ከሆነ ሞስኮ የአፀፋ ውሳኔ ልትወስን እንደምትችል ገልፀዋል፡፡