Fana: At a Speed of Life!

ጊዜን መሰረት ያደረገ ዕቅድ መጠቀሜ ውጤታማ አድርጎኛል- ተማሪ ሲፌኔ ተክሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ጊዜን መሰረት ያደረገ ዕቅድ መጠቀሜ ውጤታማ አድርጎኛል ስትል በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከ600ው 575 ውጤት ያመጣችው ተማሪ ሲፌኔ ተክሉ ገለጸች፡፡

ተማሪ ሲፌኔ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረገችው ቆይታ÷ የምፈተነውን የትምርት ዓይነትና የምዕራፍ ብዛት በመለየት እና ከጊዜ ጋር በማጣጣም በዕቅድ በማጥናቴ ውጤታማ ሆኛለሁ ብላለች፡፡

ተማሪዎች ለፈተና ሲዘጋጁ ያላቸውን ጊዜ፣ የሚሸፍኑትን የትምህርት ዓይነትና ምዕራፍ መሰረት አድርገው ዕቅድ በማዘጋጀት እንዲያጠኑም መክራለች፡፡

ፈተና ከየትኛው ምዕራፍ እንደሚመጣ ስለማይታወቅ በተቻለ መጠን ሁሉንም ምዕራፎች መሸፈን እንደሚገባም አስገንዝባለች፡፡

ለዚህ ደግሞ ጊዜ መድበው በዕቅድ ቢንቀሳቀሱ መልካም ነው፤ እኔ በዚህ ሂደት ለፈተናው ዝግጅት በማድረጌ ነው ከ600ው በሀገሪቱ ከፍተኛውን 575 ውጤት ማምጣት የቻልኩት ብላለች፡፡

ከራሷ የግል ጥረት በተጨማሪ ለተገኘው ውጤት የወላጆቿ ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ተናገራለች ፡፡

በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ “አፕላይድ ኒውትሬሽን” የማጥናት ፍላጎት እንዳላት ገልጻ÷ ተማሪዎችን ለማገዝ የተለያዩ አጋዥ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽ በዩቲዩብ ጭምር በማስተማር ላይ እንደምትገኝ ጠቅሳለች፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው እና ሜሮን ሙሉጌታ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.