የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገ-መንግስት ትርጉምና የሕገ መንግስታዊነት ክትትል ጉዳዮች ዳይሬክተርን ጨምሮ 7 ግለሰቦች በሙስና ወንጀል ተከሰሱ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህገ-መንግስት ትርጉምና የሕገ መንግስታዊነት ክትትል ጉዳዮች ዳይሬክተርን ጨምሮ ሰባት ግለሰቦች በሙስና ወንጀል ተከሰሱ።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የኤርትራ ዜግነት ካላቸው ግለሰቦች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ለምክር ቤቱ ተገቢ ያልሆኑ አስተያየቶችን በማቅረብ፣ ሀሰተኛ የዜግነት ማረጋገጫ በመጠቀም፣ የውሳኔ አፈጻጻሙን እንዳይተገበር በማድረግና በማስደረግ፣ የሀሰት ስራ ለመፈጸም የሚያገለግል ማህተም ይዞ በመገኘት በሚሉ ተደራራቢ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸዋል።
ተከሳሾቹ 1ኛ በምክር ቤቱ የህገ-መንግስት ትርጉምና ሕገ መንግስታዊነት ክትትል ጉዳዮች ዳይሬክተር ሙልዬ ወለላው፣ 2ኛ የህግ ባለሙያ ሀ/ሚካኤል ልኬ፣ 3ኛ ኤርትራዊ ዜግነት ያለው ቃላት ባህታ፣ 4ኛ ወ/ሮ አልሳቤጥ/ት ፍስሀ፣ 5ኛ የጥቅም ተጋሪ ናቸው የተባሉት ተክለማርያም ጸጋዬ ወይም አቶ ገብሩ፣ 6ኛ በምክር ቤቱ የብዝሃነት እና አንድነት ጥናት ቡድን መሪ የነበረ ገብሩ ገ/ስላሴ፣ 7ኛ አቶ መሀመድ ሰይድ ናቸው።
ተከሳሾች ላይ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የሙስና ወንጀል የምርመራ ቡድኖች በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ የምርመራ ማጣሪያ ስራ ሲያከናውን እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።
የምርመራ መዝገቡን ከፖሊስ የተረከበው ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1/ሀ፣ አንቀጽ 33 እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1/ሀ/ እና ንዑስ ቁጥር 2 ስር በተመላከተው ድንጋጌ እና በሌሎች ድንጋጌዎችንም ተላልፈዋል በማለት ክስ አቅርቦባቸዋል።
በአንደኛው ክስ 1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች ላይ ብቻ እንደተመላከተው 1ኛ ተከሳሽ በምክር ቤቱ በተለያዩ የስራ ኃላፊነትና የህገ-መንግስት ትርጉምና የሕጎች ሕገ መንግስታዊነት ክትትል ጉዳዮች ዳይሬክተር በመሆን ሲሰራ፣ የጥብቅና ባለሙያ ከሆነው ከ2ኛ ተከሳሽ እና በግል ስራ ከሚተዳደረው 3ኛ ተከሳሽ ጋር በጥቅም በመመሳጠር፣ በአካልና በስልክ በመደራደር በ1992 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለወ/ሮ አልጋነሽ ኃይሉ በጨረታ የተሰጠውን በቦሌ ክ/ከ ወረዳ 3 የሚገኝ ቤትና ይዞታን የኔ ነው በማለት የሽያጭ ውሉ እንዲፈርስ የአቶ ባህታ ትርፌ ባለቤት ነኝ የሚሉ ኤርትራዊት የሆኑ ወ/ሮ አልሳቤት ተስፋጽዮን የተባሉ ግለሰብ ክስ ባቀረቡበት ጊዜ ላይ “ከሳሽ ወ/ሮ አልሳቤት ተስፋጽዮን በአባታቸው ኤርትራዊ በእናታቸው ደግሞ ኢትዮጰያዊት ናቸው…” የሚል ሀሰተኛ ደብዳቤ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ መደረጉን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል።
በዚህ ጊዜ በ1ኛ ተከሳሽ በኩል ለምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ተገቢ ያልሆነ አስተያየት እንዲቀርብ በማድረግ 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ በጥብቅና አገልግሎት ሽፋን ተጨማሪና ከቤቱ ዋጋ የአምስት በመቶ የይምሰል የጥብቅና አገልግሎት ውል በመዋዋል ለ1ኛ ተከሳሾች ጥቅም የሰጠ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
3ኛ ተከሳሽ ውሳኔው በድጋሜ ለም/ቤቱ ሳይቀርብ እንዲፈጸም እና ቤቱን 4ኛ ተከሳሽ እንድትረከብ ለማድረግ በመስራት በአጠቃላይ የግል ተበዳይ 400 ሚሊየን ብር የሚገመት ቤት እንዲያጡ “አድርገዋል” በማለት በዋና ወንጀል አድራጊነት በስልጣን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።
2ኛው ክስ በ1ኛ፣ 2ኛ፣ 5ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን÷ 1ኛ ተከሳሽ የህገ-መንግስት ትርጉምና የህጎች ሕገ መንግስታዊነት ክትትል ጉዳዮች ዳይሬክተር በመሆን ሲሰራ፣ 6ኛ ተከሳሽ በም/ቤቱ የብዝሃነት ቡድን መሪ ሆኖ ሲሰራ፣ ከ2ኛ ተከሳሽ እና ከ5ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር ወ/ሮ ምህረት ፀጋየ ገ/መድህን የተባሉ ግለሰብ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ወረዳ 1ተብሎ በሚጠራው ስፍራ የሚገኝ 1 ሺህ 400 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መኖሪያ ቤት “በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ምክንያት ከነቤተሰቦቼ ወደ ኤርትራ ስሄድ በቃል በተደረገ የአደራ ውል ሙሉ ይዞታውን እና ቤቱን ውክልና ሰጥቼው የሄድኩት ንብረት ይመልስልኝ በማለት” በአቶ ነጋ ገ/ሐዋሪያት ላይ ክስ ከመሰረቱ በኋላ፣ አቶ ነጋ ገ/ሐዋሪያት የተባሉት ግለሰብ ደግሞ የህገ-መንግስት ትርጉም ይሰጥልኝ በማለት ለፌዴሬሽን ም/ቤት ይግባኝ ያቀርባሉ።
1ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች የወ/ሮ ምህረት ፀጋየ ገ/መድህን ባለቤት፣ ወኪል ከሆነው 5ኛ ተከሳሽ ጋር በጥቅም በመመሳጠር፣ 1ኛ ተከሳሽ አቶ ነጋ ገ/ሀዋርያት ያቀረቡት የእግድ አቤቱታ ውድቅ እንዲደረግ የውሳኔውን አፈጻጸም በልዩ ሁኔታ በመከታተል ድጋፍ ማድረግ 1ኛ፣ 2ኛ፣ 5ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች የግል ተበዳዮች ይዞታና ቤት እንዲያጡ ማድረጋቸውም በክሱ ተጠቁሟል፡፡
ኤርትራዊያኑ 5ኛ ተከሳሽ በባለቤቱ ወ/ሮ ምህረት ጸጋዬ የማይገባቸውን የማይንቀሳቀስ 1 ሺህ ካሬ ሜትር ቤትና ይዞታ ጥቅም ያለአግባብ እንዲያገኙ አድርገዋል በማለት 1ኛ እና 6ኛ ተከሳሾች በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ ናቸው ከተባሉት ከ2ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ጋር በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በሚል ተከሰዋል።
3ኛ ክስ ላይ በ1ኛ እና በ7ኛ ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን÷ ወ/ሮ መስታወት ያቀረቡትን አቤቱታ መርምሮ የህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ በአብላጫ ድምጽ ትርጉም ያስፈልገዋል በማለት ለፌዴሬሽን ም/ቤት ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ 1ኛ ተከሳሽ ስልጣኑን ያለአግባብ በመገልገል 7ኛ ተከሳሽን ለመጥቀም የውሳኔ ሀሳቡን የህገ-መንገስት ትርጉም አያስፈልግም በማለት የውሳኔ ሀሳብ በማቅረብ የቋሚ ኮሚቴ አባላትን በማሳመን፣ ወ/ሮ መስታወት በስማቸው የሚገኙትን 5ዐዐ ካሬ ሜትር ይዞታ እና ሁለት ተሽከርካሪዎችን በማሳጣት 1ኛ ተከሳሽ የማይገባውን 200 ሺህ ብር ማግኘቱ ተጠቅሶ በከባድ የስልጣን አላግባብ መገልገል ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በሌላኛው ክስ ደግሞ በ1ኛ ተከሳሽ ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን÷ በ1996 የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 390 (1) ስር የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ የፌዴሬሽን ም/ቤት ሰራተኛ በሆነችው ወ/ሮ ብርቱኳን መለሰ አለሙ ስም የተቀረጸ “ብርቱኳን መለሰ አለሙ” የሚል ማህተም በነሃሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ከረፋዱ 4፡35 ሲሆን በ1ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤት ውስጥ በብርበራ መገኘቱን ዐቃቤ ሕግ ጠቅሶ የሀሰት ስራ ለመፈጸም የሚያገለግሉ መሳሪያዎችን ይዞ መገኘት ወንጀል ተከሷል።
በ6ኛ ክስ ላይ ደግሞ 4ኛ ተከሳሽ የአቶ ባህታ ትርፌ ባለቤት ነኝ በማለት ኤርትራዊነቷን በመደበቅ ሀሰተኛ የሰነድ ደብዳቤ ለችሎቱ እንዲቀርብ በማድረግና ለ3ኛ ተከሳሽ ውክልና በመስጠት የከባድ ማታለል የሙስና ወንጀል ተከሳለች የሚል ይገኝበታል፡፡
የፌደራል ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን የክስ ዝርዝርን ተመልክተው የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ተቀጥሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከህግ ውጪ ተወስነዋል በተባሉ ሌሎች የቤቶች ጉዳዮች ላይ የምርመራ ስራው መቀጠሉን ለማወቅ ተችሏል።
በታሪክ አዱኛ