አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በመድፈኞቹ ቤት ለመቆየት የሚያስችላቸውን ውል አራዘሙ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአርሰናል አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ በክለቡ ለተጨማሪ ዓመታት የሚያቆያቸውን ውል አራዝመዋል፡፡
በዚሁ መሰረት ስፔናዊው አሰልጣኝ አርቴታ በሰሜን ለንደኑ ክለብ ለተጨማሪ ሦስት ዓመታት ለመቆየት የሚያስችላቸውን ፊርማ ማኖራቸውን አርሰናል አስታውቋል፡፡
ከፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ በኋላ በሰጡት አስተያየትም÷ ኮንትራቱን በማራዘማቸው ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ገልጸው በዚህም ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል፡፡
አሰልጣኙ በፈረንጆቹ ታኅሣስ 2019 ላይ አርሰናልን መቀላቀላቸውንም ነው ክለቡ ያስታወሰው፡፡
የአርቴታ ውል እስከ ፈረንጆቹ 2027 ድረስ በመራዘሙም ክለቡ ደስተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በ2022/23 እና 2023/24 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አርሰናል ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን÷ ይህም ከበርካታ ዓመታት በኋላ የተገኘ ከፍተኛ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡