የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት የላቀ ብቃት ያካበቱ ባለሙያዎችን ለማፍራት ማስቻሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት በሲቪልም ሆነ በሃይድሮ ሜካኒካል ሥራዎች የላቀ ብቃት ያካበቱ ባለሙያዎችን ማፍራት መቻሉ ተገለጸ።
የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኤፍሬም ወልደኪዳን (ኢ/ር)፤ ለፕሮጀክቱ ስኬት ከዲዛይን ጀምሮ እስከ ግንባታው የኢትዮጵያውያን ሚና የላቀ መሆኑን አስታውሰዋል።
የፕሮጀክቱ ግንባታ ሲጀመር በአንድ ጊዜ እስከ 15 ሺህ ዜጎች በግንባታው ሂደት ላይ በተለያዩ ሙያዎች ይሳተፉ የነበሩ ባለሙያዎች ሌት ከቀን በመትጋት ለግድቡ እውን መሆን ዘላለማዊ አሻራቸውን በማሳረፍ የሚያኮራ ተግባር ፈፅመዋል ብለዋል።
በግንባታው የረጅም ዓመት ልምድ በቀን ሰራተኝነት የጀመሩ በርካታ ወጣቶች አሁን ላይ ከፎርማን እስከ ሱፐርቫይዘርነት መድረሳቸውን አብራርተዋል።
በዚህም በሲቪልም ሆነ በሃይድሮ ሜካኒካል ሥራዎች የላቀ ብቃት ያካበቱ በርካታ ባለሙያዎችን ማፍራት ስለመቻሉ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ግድቡ 13 ተርባይኖች እንዳሉት ገልጸው፤ የጀነሬተር አካል እስከ 12 ሜትር ዲያሜትርና ከ460 ቶን በላይ ክብደት ስላለው በትራንስፖርት አጓጉዞ ለማድረስ ፈታኝ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ነገር ግን በፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን በየጊዜው አቅማቸውን በማጎልበት ዛሬ ላይ ግብዓቶችን በስፍራው እንዲገጣጠሙ ማድረግ የሚችሉበት አቅም ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
በመሆኑም በቀጣይ ኢትዮጵያ ለምትገነባቸው የሀይድሮ ፓወር ፕሮጀክቶች የሙያ ብቃትና ዝግጁነት እንዲኖር አስችሏል ሲሉ ተናግረዋል።
የግድቡ ግንባታ ሲጀመር ተቀጥረው ይሰሩ እንደነበር ያስታወሱት የኬ.ቲ ኢንዱስትሪያል ሶሉሽን ሥራ አስኪያጅ ሞላ አስማረ፤ በሂደት የራሳቸውን ድርጅት ከፍተው ለተርባይን ማቀዝቀዣ ክፍል አካል የሆነውን ራዲያተር በራሳቸው መስራት መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
አብዛኛውን የፕሮጀክቱን ግብዓት በራሳቸው መሥራት እንደሚችሉ ገልጸው፤ ከአቅም ግንባታ ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ማዳን ያስችላልም ብለዋል፡፡
በግድቡ ላይ በተለያዩ ሙያዎች ላይ የተሳተፉ በርካታ ወጣቶች በየዘርፉ የተሻለ የሙያ ደረጃ ላይ የደረሱ እንዳሉም ተናግረዋል።
በብየዳ ሥራ የተሰማሩት ወጣት ያየህ የሻንበል እና ህይወት አስማረ፣ በግንበኛ ሙያ የተሰማራችው ወጣት ደጌ በማንኛውም ቦታ በብቃት መሥራት የሚያስችል አቅም መፍጠር መቻላቸውን ገልጸዋል።