ሰሜን ኮሪያ በርካታ ቁጥር ያለው ባለስቲክ ሚሳዔል አስወነጨፈች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሜን ኮሪያ በርካታ ቁጥር ያለው የአጭር ርቀት ተወንጫፊ ባለስቲክ ሚሳዔል ማስወንጨፏ ተነገረ።
የደቡብ ኮሪያ ጥምር ጦር አዛዦች እንዳስታወቀው÷ ሰሜን ኮሪያ በቁጥር በርከት ያሉ ባለስቲክ ሚሳዔሎችን ወደ ምስራቅ ባህር ዛሬ ማለዳ ላይ ተኩሳለች።
በርካታ የአጭር ርቀት ባለስቲክ ሚሳዔሎች ከፒዮንግያንግ ተወንጭፈው በ360 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የምስራቅ ባህር ላይ ማረፋቸውን የደቡብ ኮሪያ አረጋጧል፡፡
ሚሳዔሎቹ ያረፉበት የምስራቅ ባህር ደሴት የሆነው የሰሜን ሃምግዮንግ ግዛት ላይ ነዋሪዎች የሌሉበት ሲሆን÷ ሰሜን ኮሪያ የአጭር ርቀት ተወንጫፊ ሚሳዔሎችን ለመሞከር በተደጋጋሚ የምትጠቀምበት ስፍራ መሆኑ ተገልጿል።
ይህ ሙከራ ወደ ደቡባዊ አቅጣጫ ቢደረግ እንደ ሴዑል እና ዳኤጄኦን ያሉ ዋና ዋና የደቡብ ኮሪያ ከተሞችን ሊመታ እንደሚችል ተነግሯል።
ይህ የሰሜን ኮሪያ ድርጊት ጠብ አጫሪ እና የኮሪያ ልሳነ ምድርን ሰላምና መረጋጋትን አደጋ ውስጥ የሚከት መሆኑን የደቡብ ኮሪያ ጥምር ጦር አዛዦች መግለጹን ኬቢኤስ ዘግቧል።
የባለስቲክ ሚሳዔል ሙከራውን ያደረገችው ሰሜን ኮሪያ÷ ባለፈው ሳምንት ለተከታታይ አምስት ቀናት ቆሻሻ የያዙ ፊኛዎች (ባሉን) ድንበር አቋርጠው በደቡብ ኮሪያ እንዲያርፉ ማድረጓን ዘገባው አስታውሷል።