የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ኤምባሲዎች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ተቀማጭነታቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ኤምባሲዎች አዲሱን ዓመት በማስመልከት ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ሼን ኪንሚን ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፤ ኢትዮጵያና ቻይና የራሳቸው የሆነ የዘመን አቆጣጠር ያላቸው ሀገራት መሆናቸው ልዩ እንደሚያደርጋቸውም ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ሚያን ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆን ተመኝተው ኢትዮጵያ የተዋበች ብዝሃ ሀገር ናት፤ ብዝሃ ማንነቶች ለኢትዮጵያ አንድነት ድምቀት ናቸው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አምባሳደር መሐመድ ሳሌም አል-ራሺዲ፣ በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ እንዲሁም በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር አሊ አክባር ሬዛይ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅርና የብልጽግና እንዲሆን ተመኝተዋል።
በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ አንድሪው ኦኪንደን በኢትዮጵያ ያለፈው ዓመት በርካታ መልካም ነገሮች የነበሩት ጊዜ ነው በማለት አስታውሰው፤ አዲሱ ዓመት የስኬት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር ዶክተር አቭረሃም ንጉሴ፣ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክሲስ ላሜክ እና በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ጁሊያ ኒብሌት ለመላው ኢትዮጵያውያን መልካም አዲስ ዓመት እንዲሆን በመመኘት መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሕንድ፣ ኮሪያ ሪፐብሊክ፣ ኦስትሪያ፣ ስዊድን፣ ጀርመን፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ሞሮኮና ሜክሲኮ በኤምባሲዎቻቸው በኩል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡