ካናዳ ለኢትዮጵያ የ14 ሚሊየን የካናዳ ዶላር ድጋፍ አደረገች
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የካናዳ መንግስት ለኢትዮጵያ የቀድሞ ታጣቂዎችን መልሶ የማቋቋም መርሐ-ግብር የ14 ሚሊየን የካናዳ ዶላር ድጋፍ ማድረጓን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
መርሐ-ግብሩ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ መልሶ ማቋቋም ኮሚሽን፣ ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) እና ከበርካታ ለጋሾች ጋር በመተባበር እየተተገበረ ነው።
ዩኤንዲፒ ለመርሐ-ግብሩ ድጋፉን እንዲያስተባብር በተባበሩት መንግስታት ትእዛዝ መሰጠቱ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ጆሹዋ ታባህ እንዳሉት ፥ ሁለገብ ትጥቅ የማስፈታትና መልሶ የማቋቋም መርሐ ግብር ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ወሳኝ ነው።
መርሐ-ግብሩ የተነደፈው የቀድሞ ታጣቂዎችን፣ ማህበረሰቦችን እና መላው ኢትዮጵያ ከነበሩበት ችግር እንዲያገግሙና መልሰው የመገንባትን ዓላማ ለመደገፍ ነው ብለዋል፡፡
በዚህም መርሐ-ግብሩ በአፋር፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና በትግራይ ክልሎች ያሉ የቀድሞ ታጋዮችን ያግዛልም ነው የተባለው።
የብሄራዊ መልሶ ማቋቋሚያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን ፥ ለድጋፉ ምስጋናቸውን አቅርበው ፤ ድጋፉ ለታሰበለት ዓላማ ይውላል ብለዋል፡፡