ጠላቶቻችን የሚያሥቀምጡብንን መሠናክል ጥሰን ለማለፍ ፅናትና ቁርጠኝነት መሰነቅ ይኖርብናል – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2016 (ኤፍ ቢሲ) ጠላቶቻችን የሚያሥቀምጡብንን መሠናክል ጥሰን ለማለፍ ፅናትና ቁርጠኝነት መሰነቅ ይኖርብናል ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የ2017 ዓ/ም አዲስ አመትን አስመልክቶ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሙሉ መልዕክቱ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ጷጉሜ 05 ቀን 2016 ዓ.ም
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተከበራችሁ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት አመራሮች አባላትና ሲቪል ሠራተኞች ለ2017 አዲስ አመት እንኳን በሠላም አደረሳችሁ አደረሰን። አዲሱ አመት የሠላም የጤና እና የስኬት ዘመን እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።
2016 ዓ.ም በፈተና ውስጥ ሆነን በርካታ ስኬቶችን ያሥመዘገብንበት መሆኑ አመቱን ልዩ ያደርገዋል። ሀገራችንን በነውጥ ለማፍረስ እና የልማት ጉዟችንን ለማደናቀፍ ታስቦ ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ባሉ ፀረ ሠላም ሀይሎች ቀስቃሽነት ግጭቶች በብዛት እና በተከታታይነት የተካሄዱበት ጊዜ እንደነበር አይዘነጋም። ቢሆንም ግን ሠራዊታችን ከፀጥታ ሃይሎች እና ከህዝባችን ጋር በመሆን ባካሄዳቸው ስምሪቶች በሀገራችን ላይ ተደቅነው የነበሩትን የህልውና አደጋዎች መቀልበስ ተችሏል።
በ2017 ዓ.ም ከ2016 ዓ.ም በተሻለ በሀገራችን ሠላም ሠፍኖ ሙሉ ትኩረታችን ለሀገር ዕድገት መሥራት ላይ እንድናደርግ አሁን በእየክልሉ ተበታትነው እና የሽፍታነት ተግባር ላይ ተሠማርተው የህዝቡን ሥቃይ ለማራዘም የሚሠሩትን ቡድኖች አድኖ ሙሉ በሙሉ ለመደምሰስ ሠራዊታችን ፣የፀጥታ ሃይሎች ፣የመስተዳድር አካላትና መላው ህዝባችን ከእስከዛሬው በላቀ መልኩ ተቀናጅተን እንድንሠራ በዚሁ እገልፃለሁ።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬታማነት፣ የባህር በርና ሌሎች ብሄራዊ ጥቅሞቻችንን ለማሥከበር በምናደርገው ርብርብ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ባስመዘገብንበት በአሁኑ ወቅት ታሪካዊ ጠላቶቻችን ሊያደናቅፉን ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ። በመሆኑም ይህንኑ ተገንዝበን የሚያሥቀምጡብንን መሠናክል ጥሰን ለማለፍ ፅናትና ቁርጠኝነት መሰነቅ ይኖርብናል።
በመጨረሻም ለጋራ ህልውናችን በፅናት እንድንቆም እያልኩ በዚህ ረገድ ሠራዊታችን ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ ዝግጁነቱን አጠናክሮ መቆሙን ለማረጋገጥ እወዳለሁ።
በድጋሜ መልካም አዲስ አመት