ሰላሙን በማጽናት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ይሰራል – ወ/ሮ ዓለሚቱ ኡሞድ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተገኘውን ሰላም በማጽናት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ይሰራል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕስ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሯ የ2017 ዓ/ም አዲስ ዓመትን አስመልክቶ ለክልሉና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሰላም፣ የጤናና የብልጽግና ዓመት እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በአዲሱ ዓመት ያለውን ሰላም በማጠናከር የህዝቡን መሰረታዊ ችግሮች በሚፈቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያ ዘርፎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በክልሉ ሠላምን ለማረጋገጥ እና ልማትን ለማስቀጠል እየተከናወኑ ካሉ ሥራዎች ጎን ለጎን ለህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ተጀምረው ሳይጠናቀቁ የቆዩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
እንደሀገር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ በክልሉ ስኬታማ ለማድረግ በግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
የክልሉ ህዝብ የተገኘውን ሰላም በማጠናከር የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች እውን እንዲሆኑ ተሳትፏቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።