Fana: At a Speed of Life!

በአዲሱ ዓመት በግጭት ላይ የሚገኙ ወገኖች ሁሉንም አሸናፊ ወደሚያደርገው ምክክር ሊመጡ ይገባል – መስፍን አርአያ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲሱ ዓመት በግጭት ላይ የሚገኙ ወገኖች ሁሉንም አሸናፊ ወደሚያደርገው ምክክር ሊመጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ(ፕ/ር) ጥሪ አቀረቡ።

ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በኢትዮጵያና በመላው ዓለም ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የእንኳን ለአዲስ ዓመት አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኮሚሽኑ በ2016 ባወጣው መርሐ- ግብር መሰረት በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑንም ገልጸዋል።

በዚህም ከሚሽኑ አጀንዳ ለመሰብሰብ ተሳታፊዎችን ከወረዳ ጀምሮ በመለየት ወደ ሚቀጥለው ደረጃ ያስመረጠበት መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም ከክልል ተሳታፊዎች ጋር በመሆን አጀንዳ እየሰበሰበ የመጣበት ጊዜ እንደነበር ጠቁመዋል።

በቀጣይም በተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዚህ ታሪካዊ ሂደት ውስጥ በሙሉ ልብ እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሀገር ውስጥም በተለያዩ ምክንያቶች በግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች ሁሉንም አሸናፊና ተጠቃሚ ወደሚያደርገው ምክክር እንዲመጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በአዲሱ ዓመት ሁሉንም ስሜቶቻችንን ወደ አመክንዮ በመቀየር ለሀገራችን የምንመክርበት ጊዜ ሊሆን እንደሚገባም አመላክተዋል።

2017 ዓ.ም የሰላምና ከሁሉም በላይ የመተሳሰብ ጊዜ መሆን እንዳለበት መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.