Fana: At a Speed of Life!

በመጪዉ ዓመት በተሻለ መሠረት ላይ ቆመን የላቀ ስኬት ለማስመዝገብ የጠሩ ዕቅዶችን ይዘናል – መንግስት

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪዉ አዲስ ዓመት በተሻለ መሠረት ላይ ቆመን የላቀ አፈጻጸምና ስኬት ለማስመዝገብ የጠሩ ዕቅዶችን ይዘናል ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አዲስ ዓመትን አስመልክቶ እንደሚከተለው መልዕክቱን አስተላልፏል፡-

ለመላው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንኳን ለ2017 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ!

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመትን በጉጉት ይጠብቃሉ፤ ጋራ ሸንተረሩም የዚህ አዲስ ዓመት ጠባቂ ይመስል ኩልል ባለ ንጹሕ የምንጭ ውኃ ፏፏቴ፣ በልዩ ልዩ ኅብረ ቀለማት አበቦች ይዋባሉ፡፡ አዲስ ዓመታችን ዐዳዲስ ዕቅዶችን መተግበር የምንጀምርበት፣ ተነፋፍቀዉ የከረሙ ተማሪዎችና መምህራን በጉጉት የሚገናኙበት፣ በመኸር የተዘራዉ የሚያሸትበት፣ ዐዲስ ተስፋና ጉጉት የሚፈነጥቅበት ነው፤ ለዚህም ነው በላቀ ጉጉት የሚጠበቀው፡፡

የተጠናቀቀዉ 2016 ዓ.ም በፈተናዎች ውስጥ ብዙ ስኬቶችን አስመዝግበንበታል፡፡ ለዘመናት ለመነጋገር ነውር የነበረዉን የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ በአጀንዳነት አንሥተን መሻታችን እንዲሳካ መንገድ ከፍተናል፡፡

ከዘርፈ ብዙ ትብብር አንጻር የብሪክስ አባልነትን ጠይቀን አሳክተንበታል፡፡ የሕዳሴ ግድባችንን ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ አድርሰን ተጨማሪ ተርባይኖች ታዳሽ ኃይል እንዲያመነጩ አስችለንበታል፡፡በጀመርናቸው የግብርና ዘርፍና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች በተለይም በአረንጓዴ ዐሻራ ንቅናቄያችን ዓለማቀፍ ሽልማቶችን አሸንፈንበታል፡፡
በሀገር ውስጥ የነበሩ የሰላምና ፀጥታ ችግሮችን በሀገር በቀል እሴቶቻችንና አፍሪካዊ መፍትሔዎችን ተከትልን፣ ከዚያ አለፍ ያሉትን ደግሞ በሕዝባችን ትብብርና የፀጥታ ኃይላችን ትጋት በተሰራው ሕግ የማስከበር ሥራ ፀረ-ሕዝብ ታጣቂ ሃይሎች ለሀገር ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህም ኅብረተሰቡ ወደ ቀየዉ ተመልሶ ወደ መደበኛ ሕይወት ገብቷል፡፡ በግጭቶች ውስጥ ይሳተፉ ከነበሩ ኃይሎችም መንግሥት ያቀረበዉን የሰላም አማራጭ ጥሪን ተቀብለው፣ የተሐድሶ ሥልጠና እግኝተው በቁጭት ሕዝባቸዉን ለመካስ ወደ ማኅበረሰቡ ተቀላቅለዋል፡በጀመርነው ሀገራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትሕ ደግሞ ወደ ዘላቂና አወንታዊ ሰላም በዐዲሱ ዓመት እንደምንገባ ተስፋ ሰንቀናል፡፡

2016 ዓ/ም የግብርና ሥራችን ከዝናብ ወቅት በተጨማሪ በበጋ መስኖ የላቀ ስኬት ያስመዘገበበት ዓመትም ነበር፡፡ በአረንጓዴ ዐሻራ የተከልናቸው አትክልትና ፍራፍሬዎች በከፍተኛ ደረጃ ምርት መስጠት የጀመሩበት፤ ዘንድሮም የራሳችንን ክብረ ወሰን አሻሽለን በአንድ ጀምበር ከ615 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን የተከልንበትና በለውጡ ዓመት በአጠቃላይ ከ40 ቢሊዮን ችግኞች በላይ ያደረስንበት ዓመት ነበር፡፡ በሌማት ትሩፋት ንቅናቄያችን የጓሮ አትክልትና እንስሳት ርባታ ላይ በማተኮር መሠረታዊ ለውጥ አምጥተንበታል፡፡ በዚህም የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና የሥነ ምግብ ሁኔታችንን ማሻሻል ችለናል፡፡

በዚህ በተጠናቀቀው ዓመት በኢንዱስትሪ ዘርፉም ስኬት አስመዝግበናል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመዉ የነበሩ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ ተመልሰዋል፤ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችም ተከፍተዋል፡፡ የተኪ ምርትና የኢትዮጵያን ይሸምቱ ንቅናቄዎችም ፍሬያማ ነበሩ፡፡ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ወደተለያዩ ሀገራት የመላክ ጅምሮች ተስፋ ሰጪ ውጤት አሳይተውናል፡፡በዲጂታል ዘርፉ ትልቅ ዐልመን ትልቅ ንቅናቄ ውስጥ ገብተናል፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ “ኮደሮችን” ሥልጠና አስጀምረናል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በተሟላ መልኩ መተግበር ጀምረንበታል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የነበሩ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ አስገብተን የቱሪዝም ዘርፋችንን ተጨማሪ እሴት አጎናጽፈንበታል፡፡

በአጠቃላይ 2016 ዓ.ም በበርካታ ስኬቶች ያጠናቀቅነዉ ዓመት ሆኗል፡፡ በመጪዉ አዲስ ዓመት ደግሞ በተሻለ መሠረት ላይ ቆመን የላቀ አፈጻጸምና ስኬት ለማስመዝገብ የጠሩ ዕቅዶችን ይዘናል፡፡ በዚህ ላይ የመላዉ ሕዝባችን ተስፋና ርብርብ ሲታከልበት አዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያችን የሰላም፣ የፍቅር፣ የደስታ፣ የብልጽግና ዘመን እንዲሆን እንመኛለን፡፡

በድጋሜ እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሠላም አደረሳችሁ!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.