Fana: At a Speed of Life!

የቅባት እህሎችን ወጪ ንግድ ለማሳደግ የዘርፉን አቅም በሚገባ መጠቀም እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ወጪ ንግድን ለማሳደግ የዘርፉን አቅም በሚገባ መጠቀም እንደሚገባ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴዔታ ያስሚን ወሃብረቢ እንዳሉት÷ኢትዮጵያ አሁን ካላት የጥራጥሬና ቅባት እህሎች እምቅ ሃብት አንጻር የምታገኘው ገቢ አነስተኛ ነው፡፡

ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ወጪ ንግድ 18 በመቶውን እንደሚይዝም አስረድተዋል፡፡

ስለሆነም ከዘርፉ የሚገኘውን የወጪ ንግድ ገቢ ለማሳደግ በሀገሪቱ ያለውን እምቅ ሃብት አሟጥጦ መጠቀም እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም በዘርፉ የተሰማሩ ባለድርሻ አካላት በትብብርና በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት፡፡

የኢትዮጵያ ጥራጥሬ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ኤዳዎ አብዲ በበኩላቸው÷ማህበሩ ከ500 በላይ የዘርፉ አምራችና ላኪ ማህበራትን እንዳቀፈ አንስተዋል፡፡

በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችንና ዕድሎችን አስመልክቶ ከአምራቶች፣ ላኪዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ በትብብር ለመስራት መግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ንግድ፣ የተዛባ የንግድ ሰንሰለት፣ የሰላም እና የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት የዘርፉ ዋና ዋና ተግዳሮቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይ ለሀገሪቱ ሁነኛ የገበያ ምንጭ አማራጭ ተደርገው ወደ ውጭ የሚላኩት የጥራጥሬና ቅባት እህሎችን መጠን ለማሳደግም በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

Screenshot

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.