Fana: At a Speed of Life!

አቶ ሙስጠፌ በአዲሱ ዓመት ከተረጂነት ለመላቀቅ የተጀመሩ ስራዎች እንደሚጠናከሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲሱ ዓመት ከተረጂነት ለመላቀቅና በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመሩ የስንዴና የሩዝ ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ገለጹ።

አቶ ሙስጠፌ አዲሱን የ2017 ዓመት አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም÷ በተጠናቀቀው ዓመት እንደ ሀገር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ የተካሄደበት እና ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ የሆነበት ዓመት እንደነበረ አንስተዋል።

“በዓመቱ ከተሞቻችንን ለማዘመን ከፍተኛ ጥረት የጀመርንበት ነው” ያሉት አቶ ሙስጠፌ÷ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ መልካም ጅምሮች የታዩበት ዘመን እንደነበርም አንስተዋል፡፡

በተለይም በተጠናቀቀው ዓመት የክልሉን ህዝብ ከተረጂነት ለማላቀቅና በምግብ ራስን ለመቻል የተጀመሩ የስንዴና ሩዝ ልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እና በገቢ አሰባሰብ እንዲሁም በስራ እድል ፈጠራ ክልሉ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸው÷ እነዚህ ስራዎች በአዲሱ ዓመትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

በክልሉ የተገኘውን ሰላምና መረጋጋት በማጠናከር በአሸባሪ ሀይሎች ሊፈጸሙ የሚችሉ ትንኮሳዎችን አስቀድሞ ለመከላከል የፀጥታ መዋቀሩ ከህዝብ ጋር የሚያደርገው ትብብርም በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ አዲሱ ዓመት የአንድነት፣ የሰላም፣ የደስታና የስኬት ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.