ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ በአዲሱ ዓመት የሠራዊታችን የማድረግ አቅም የበለጠ እናሳድጋለን አሉ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲሱ ዓመት የሠራዊታችንን የማድረግ አቅም የበለጠ ለማሳደግ ዘመናዊ የሎጂስቲክስ የትጥቅ አቅማችንን የምናሳድግበትና የምናዘምንበት ዓመት ይሆናል ሲሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል አስታወቁ፡፡
ኮሚሽነር ጀኔራሉ አዲሱን ዓመት አስመልክተው የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና የኢትዮጵያ ፖሊስ እንኳን ለ2017 ዓ.ም አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ የሚታዩና የሚጨበጡ ስኬቶችን ማስመዝገቡንም አንስተዋል፡፡
በዚህም በወንጀል መከላከል፣ በወንጀል ምርመራ፣ በሰው ኃይል ልማት፣ በቴክኖሎጂ፣ በስልጠናና ትምህርት እንዲሁም በሌሎች ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ውጤታማ እና አኩሪ ሥራዎችን መሥራቱን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማደጉን እና የልዩ ፀረ-ሽብር መምሪያ ኮማንዶ ኃይልም የሚሰጠውን ግዳጅ በብቃት እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አዲሱ አመት የሠራዊታችን የማድረግ አቅም የበለጠ ለማሳደግ ዘመናዊ የሎጂስቲክስ የትጥቅ አቅማችንን የበለጠ የምናሳድግበትና የምናዘምንበት ዓመት ይሆናል ነው ያሉት፡፡
በ2016 ዓ.ም በርካታ ድሎችን የተጎናፀፍንበት እና የሀገራችን ሰላም እየተሻሻለ የመጣበት ዓመት ነበር ማለታቸውን የፌዴራል ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡