በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የምንጊዜም ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበው ተማሪ…
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የቃላሚኖ ልዩ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪው ዮናስ ንጉሰ በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና 675 በማምጣት በደረጃው የምንጊዜውንም ከፍተኛ ውጤት አስመዝግቧል፡፡
በተመሳሳይ ተማሪ ሔለን በርኸ ከቃላሚኖ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 662 በማምጣት ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡት ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት፡፡
ዮናስ ንጉሰ እና ሔለን ባለፉት ዓመታት ያጋጠሟቸ ሁለት ፈተናዎች ኮቪድ-19 እና የሰሜኑ ጦርነት በትምህርታቸው ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሮ ማለፉን ይናገራሉ፡፡
በእነዚያ ጊዜያት የባከነውን ጊዜያቸውን በውጤት ለመካስ ጠንክሮ መስራትን መምረጣቸውን ነው የገለጹት፡፡
ተማሪዎቹ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ ባስመዘገቡት ውጤት መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
በቃላሚኖ ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በ2016 ዓ.ም ለፈተና ከተቀመጡ 282 ተማሪዎች መካከል በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛው ውጤት የተመዘገበው በተማሪ ዮናስ ንጉስ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የተማሪ ዮናስ ውጤትም እስካሁን ከነበሩት ውጤቶች ሁሉ ከፍተኛ መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት፡፡
ሽረ እንደስላሴ ተወልዶ ያደገው ተማሪ ዮናስ ትምህርት ከየትኛውም ጫና ነፃ መሆን እንዳለበት እና በትምህርት ላይ የሚደርሰው ጉዳት እንደ ሀገር ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ ተማሪ ሔለን በርኸ ከቃላሚኖ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 662 በማስመዝገብ ከፍተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች መካከል አንዷ ናት፡፡
ለዚህ ውጤት መመዝገብ የቃላሚኖ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ያደረገላቸው እገዛ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ ተማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
በሰለሞን ይታየው