Fana: At a Speed of Life!

በሕገወጥ መንገድ ከ56 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የመንግስት ይዞታን እንዲወሰድ በማድረግ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተከሰሱ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ በሕገወጥ መንገድ ከ56 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የመንግስት ይዞታ እንዲወሰድ አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ የመንግስት ሰራተኞችና ግለሰቦች ተከሰሱ።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ በተለያዩ ቦታዎች አርሶ አደርና የአርሶ አደር ቤተሰብ በሚል ምክንያት የሊዝ ዋጋው ከ56 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ 3 ሺህ 52 ካሬ ሜትር የመንግስት ይዞታን ግለሰቦች በህገወጥ መንገድ መብት እንዲፈጠርላቸው አድርገዋል የተባሉና ይዞታውን በመውሰድና ለግል ጥቅም አውለዋል የተባሉ አጠቃላይ 15 ሰዎች ላይ ነው ክስ የተመሰረተው፡፡

ክሱ የተመሰረተው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ወንጀል ችሎት ነው።

ክስ ከተመሰረተባቸው መካከል÷ 1ኛ የቀድሞ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ የወረዳ 11 ዋና ስራ አስፈፃሚ የነበረው መልካሙ በቃና፣ 2ኛ በክፍለ ከተማው የወረዳ 12 ዋና ስራ አስፈፃሚ የነበረው ሶቨት አበበ፣ 3ኛ የወረዳ 11 መሬት ልማት አስተዳደር ጽ/ቤት የውል ሰነዶች አጣሪ ወሳኝ ባለሙያ ታያቸው ጥበብ መሆናቸው ተጠቅሷ፡፡

እንዲሁም 4ኛ በክፍለ ከተማው የመሬት ልማት አስተዳደር ፅ/ቤት የመስክ ልኬት ሽንሻኖና ካርታ ዝግጅት የቴክኒክ ባለሙያ ማህሌት ጋሼ፣ 5ኛ የወረዳ 1 መሬት ልማት አስተዳደር ፅ/ቤት የመስክ ልኬት ሽንሻኖና ካርታ ዝግጅት ባለሙያ ሰብለ በቀለ እና ደላላ ነው የተባለው ፉፋ በዳዳ ይገኙበታል።

ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾች ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1/ሀ ፣ አንቀጽ 33 እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣዉን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1/ሀ/ እና ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፋቸውን በየተሳትፎ ደረጃው ጠቅሶ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸዋል።

በዚህም ከ1ኛ እስከ 6ኛ ያሉ ተከሳሾች እንደቅደም ተከተላቸው በክፍለ ከተማው ወረዳ 11 ውስጥ ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ የክፍለ ከተማ መሬት ይዞታና አስተዳደር ጽ/ቤት የውል ሰነዶች አጣሪና ወሳኝ ባለሙያ፣ የመስክ ልኬት ሽንሻኖና ካርታ ዝግጅት ቴክኒክ ባለሙያ፣ የመብት ፈጠራ ቡድን መሪ፣ የመስክ ልኬት ሽንሻኖና ካርታ እና የጂ.አይ.ኤስ ባለሞያ ሆነው ሲሰሩ ከ7ኛ እስከ 15ኛ ካሉ ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር በህገ ወጥ መንገድ ባለይዞታ ላልሆኑና በመሬቱ ላይ መብት ለሌላቸው ከ7ኛ እስከ 15ኛ ላሉ ተከሳሾች፣ አርሶ አደርና የአርሶ አደር ልጅ ሳይሆኑ በሐሰተኛ የአርሶ አደር ኮሚቴ ቃለ ጉባኤና በሰነዶች መብት እንዲፈጠር አድርገዋል በማለት ዐቃቤ ሕግ በዝርዝሩ ጠቅሷል።

በዚህም ከ7ኛ እስከ 15ኛ የተጠቀሱ ተከሳሾች አርሶ አደር እና የአርሶ አደር ልጅ ሳይሆኑ 7ኛ ተከሳሽ 500 ካሬ ሜትር ባዶ ቦታ፣ 8ኛ ተከሳሽ 418 ካሬ ሜትር፣ 9ኛተከሳሽ 418 ካሬ ሜትር 10ኛ ተከሳሽ 418 ካሬ ሜትር ባዶ ቦታ፣ 11ኛ ተከሳሽ 270 ካሬ ሜትር 12ኛ ተከሳሽ 418 ካሬ ሜትር፣ 13ኛ ተከሳሽ 200 ካሬ ሜትር 14ኛ ተከሳሽ 200 ካሬ ሜትር 15ኛ ተከሳሽ ደግሞ 210 ካሬ ሜትር ይዞታ በመውሰድ አማካይ ወቅታዊ የሊዝ ጨረታ ዋጋዉ ብር 56 ሚሊየን 25 ሺህ 519 ብር ከ92 ሳንቲም የሆነ የመንግስት ይዞታ ላይ በተለያዩ ቀናቶች በህገ ወጥ መንገድ መብት እንዲፈጠርላቸው እንዳደረጉም ተጠቅሷል፡፡

በዚህም ቦታውን እንዲወስዱ በማድረግ እና በዚሁ መጠን በመንግስት ላይ ጉዳት እንዲደርስ የተደረገ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሶ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ያሉ ተከሳሾች በዋና ወንጀል አድራጊነት እንዲሁም ከ7ኛ እስከ 15ኛ ያሉ ተከሳሾች በልዩ ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ስልጣን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡

በዚህ መልኩ በዐቃቤ ሕግ የቀረበው ዝርዝር ክስን ተረኛ ችሎቱ ለተወሰኑ ተከሳሾች እንዲደርስ በማድረግ፣ ያልቀረቡ እንዲቀርቡ በማለት በመደበኛው ችሎት ለጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.