Fana: At a Speed of Life!

ከ1 ቶን በላይ የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች ከመስከረም 2 ጀምሮ በስራ መግቢያና መውጫ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ1 ቶን በላይ የሚጭኑ ተሽከርካሪዎች ከመስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በስራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት መንቀሳቀስ እንደማይችሉ የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

በመዲናዋ በስራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ እና የአየር ብክለትን ለመቀነስ እንዲሁም የጭነት፣ ማሽነሪዎችን እና መሰል ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ለመወሰን መመሪያ ቁጥር 149/2016 መውጣቱ ተነግሯል ፡፡

መመሪያው ወደ ከተማዋ የሚገቡና በከተማ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም ከተማዋን አቋርጠው በሚያልፉ ከ1 ቶን ወይም ከ10 ኩንታል በላይ የመጫን አቅም ያላቸው የተለያዩ የፈሳሽና የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች እና የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡

በዚህም ማንኛው የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪ እና የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ 3 ሰዓት እንዲሁም ከሰዓት በኋላ ከቀኑ 10 ሰዓት ተኩል እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ወደ ከተማዋ ውስጥ መግባትም ሆነ በከተማዋ መንቀሳቀስ ተከልክሏል።

ጭነት መጫንም ሆነ ማራገፍ እንዲሁም በዋና ዋና የትራፊክ ፍሰት በሚበዛባቸው መንገዶች ላይ መቆም የተከለከለ መሆኑንም ባለስልጣኑ አስገንዝቧል።

ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ላይ እያሉ የጊዜ ገደብ ሰዓት ከደረሰባቸው በከተማዋ መግቢያ በሮች ላይ ከዋና መንገድ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቦታ ላይ የአካባቢውን የትራፊክ እንቅስቃሴ በማያውክ መልኩ በመቆም የሰዓት ገደቡ እስኪያልፍ መጠበቅ አለባቸው ተብሏል፡፡

ባለስልጣኑ በመመሪያው ከተደነገገው ሰዓት ውጭ እንዲሁም እሁድ እና የበዓል ቀናት ማንኛውም የጭነት ተሽከርካሪ ወይም የኮንስትራክሽን ማሽነሪ ወደ ከተማዋ ውስጥ መግባትም ሆነ መንቀሳቀስ እንዲሁም ጭነት መጫን እና ማራገፍ ይችላል ብሏል ፡፡

ሰሌዳቸው በሀገር መከላከያ ወይም በፖሊስ የተመዘገበ የሀገር መከላከያ እና ሌሎች የጸጥታ ስራዎችን የሚያከናውኑ፣ የድንገተኛ አደጋ የሚሰሩ ቀላልና ከባድ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ነዳጅ የሚያመላልሱ ቦቴዎች ክልከላው አይመለከታቸውም ተብሏል ፡፡

በተከለከለ ሰዓት በዋና ዋና መንገዶች ላይ የቆመ 10 ሺህ ብር፣ በዋና ዋና መንገድ ላይ የተንቀሳቀሰም ሆነ የጭነት መጫንና ማውረድ ተግባር የፈጸመ ወይም የኮንስትራክሽን ስራ የሰራ 20 ሺህ ብር እንዲሁም በመመሪያው የተደነገገውን ቅጣት በመተላለፍ ከተቀጣ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ያጠፋ ከዚህ በላይ የተገለጹ ቅጣቶችን በዕጥፍ እንደሚከፍል ነው ባለስልጣኑ ያስጠነቀቀው፡፡

ባለስልጣኑ ይህ መመሪያ ከመስከረም 2/2017 ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጾ፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጭነት፣ ማሽነሪዎች እና መሰል ተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ ለመወሰን የወጣ መመሪያ ቁጥር 38/2013 በዚህ መመሪያ መሻሩንም ባለስልጣኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አስታውቋል፡፡

በመሳፍንት እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.