Fana: At a Speed of Life!

አትሌት ጽጌ ድጉማ ለኢንቨስትመን የሚውል 1 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ተሰጣት

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ለአትሌት ጽጌ ድጉማ የእውቅናና የምስጋና መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻደሊ ሀሰን÷አትሌት ጽጌ በኢትዮጵያ ባልተለመደውና ብዙም በማንታወቅበት አጭር ርቀት ላስመዘገበችው ውጤት ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡

የአትሌቷ ውጤት ክልሉ በስፖርቱ ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም ያስመለከተ ትልቅ ስኬት ነው ሲሉም አውስተዋል፡፡

የጽጌ ድጉማ ውጤት በክልሉ የዘርፉን ባለሙያዎች በትኩረት እንዲሰሩ የቤት ስራ የሚሰጥ፤ ለተተኪ ትውልዶችም መነቃቃትን የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

አትሌቷ ላስመዘገበችው ውጤትም በአቶ አሻደሊ ሀሰን በኩል ለአትሌቷ በአሶሳ ከተማ ለኢንቨስትመን የሚውል 1 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ተበርክቶላታል፡፡

በተጨማሪም የክልሉ መለያ የሆነው ወርቅ ለወርቅ ልጆች በሚል ለአትሌቷና ለአሰልጣኟ የወርቅ ስጦታ መበርከቱን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመልክቷል፡፡

አትሌቷ ከዚህ በፊት ካስመዘገበቻቸው ውጤቶች በተጨማሪ በ33ኛው የፓሪስ ኦሊምፒክ በሴቶች በ800 ሜትር የብር ሜዳሊያ ማምጣቷ ይታወቃል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.