Fana: At a Speed of Life!

ከአጠቃላይ ተፈታኞች 36 ሺህ 409 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናን አልፈዋል- ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ 674 ሺህ 823 ተማሪዎች ያለፉት 36 ሺህ 409 መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ÷ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ይፋ መደረጉን እና ተማሪዎችም ከሌሊቱ 6 ሠዓት ጀምረው ውጤታቸውን መመልከት እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡

በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች የነበረው የደንብ መተላለፍ ከአለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ እንደነበርም አንስተዋል፡፡

የደንብ ጥሰት የፈጸሙ 313 ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ውጤታቸው እንደተሰረዘ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች ፈተና ያልወሰዱ ተማሪዎች ከመስከረም 13 እስከ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ፈተና እንደሚወስዱ ጠቁመዋል።

አዳሪ ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን በመግለጽ÷ 1 ሺህ 363 ትምህርት ቤቶች ምንም ተማሪ አላሳለፉም ብለዋል፡፡

ፈተናውን ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል ሀገራዊ አማካኝ ውጤት 29 ነጥብ 76 መሆኑን ጠቅሰው÷ የዘንድሮው ከፍተኛ ውጤት ከ700ው 675 መሆኑን እና ይህም በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘ ከፍተኛ ውጤት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም ከ600 ከተፈተኑት ውስጥ 575 ከፍተኛው ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በየሻምበል ምኅረት፣ መሳፍንት እያዩ እና ታሪኩ ወ/ሰንበት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.