መከላከያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አበረታች የግብርና ስራ እያከናወነ ነው – አይሻ መሀመድ (ኢ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የመከላከያ ተቋማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያለው የግብርና ስራ አበረታች መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ(ኢ/ር) ገለጹ።
በመከላከያ ሚኒስትሯ የተመራ ቡድን ከጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድና ሌሎች የክልሉና የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ጋር በመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽንና በዕዞች እየለማ ያለውን እርሻ ተመልክተዋል።
በዳሎል ማዕከላዊ ዕዝና የመከላከያ ሰራዊት ፋውንዴሽን በጋምቤላ ክልል 1 ሺህ 800 ሄክታር መሬትን በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን መቻሉ ተገልጿል፡፡
ሚኒስትሯ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፥ የመከላከያ ሰራዊት ተቋም የሀገርን ዳር ድንበር ከመጠበቅ በተጨማሪ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያለው የግብርና ስራ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።
መከላከያ ትልቅ አቅም ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ የግብርና ኢንቨስትመንት ዘላቂነት እንዲኖረው ይሰራል ብለዋል።
በቀጣይም በጋምቤላ ክልል በመጠን የበዛ ሄክታር መሬት በዘመናዊ መንገድ ለማልማት መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ተቋሙ የግብርና ዘርፉን ከማጠናከር ባሻገር በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ተግባራትን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው፥ የመከላከያ ሰራዊት ሰላም ከማስከበር ጎን ለጎን በክልሉ የሚያከናውናቸው የግብርና ስራዎች አቅም ከማሳደግ ባለፈ ማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማድረግ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
በክልሉ ያሉ ሰፋፊ እርሻዎች በሰብል እንዲሸፈኑ የማድረግና ዘርፉ እንዲዘምን መንግስት በትኩረት እንደሚሰራም ከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።