Fana: At a Speed of Life!

የአየር መንገዱን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል በመንቀሳቀስ ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል ተንቀሳቅሰዋል ተብለው በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ 6 ግለሰቦች ላይ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ክስ መመስረቻ ጊዜ ተፈቀደ።

የፌደራል መርማሪ ፖሊስ የምርመራ ቡድን ዮሃንስ ዳንኤል (ጆን ዳንኤል)፣ አማኑኤል መውጫ፣ ናትናኤል ወንድወሰን፣ ኤልያስ ድሪባ፣ ይዲድያ ነጻነት እና እሌኒ ክንፈ በተባሉ ግለሰቦች ላይ ሲያከናውን የቆየውን የምርመራ ማጣሪያ ስራ አጠናቆ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ማስረከቡን ለጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ አስታውቋል።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዐቃቤ ህግ በችሎት ተሰይሞ የምርመራ መዝገቡን ከፖሊስ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም መረከቡን ጠቅሶ፤ ማስረጃ ተመልክቶ ክስ ለማቅረብ እንዲያስችለው ክስ ለመመስረቻ ጊዜ አምስት ቀን እንዲሰጠው ጠይቋል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች በበኩላቸው “ዐቃቤ ህግ ምርመራውን ሲመራ ቆይቶ እንደአዲስ መዝገቡን ተመልክቼ ክስ ለመመስረት፣ ለመወሰን እንዲያስችለኝ የክስ መመስረቻ ጊዜ ይሰጠኝ ማለቱ” ተገቢ አይደለም በማለት ተከራክረዋል።

ጠበቆቻቸው ደንበኞቻቸው ተጨማሪ ጊዜ በእስር ሊቆዩ እንደማይገባ ገልጸው፤ የዋስ መብታቸው እንዲከበር ጠይቀዋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን የመረመረው ጊዜ ቀጠሮ ችሎቱ ዐቃቤ ህግ ክስ የመመስረቻ ጊዜ መፍቀድ ስነ ስርዓታዊ መሆኑን በማመን የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ በማለፍ ለዐቃቤ ህግ የአምስት ቀን የክስ መመስረቻ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.