Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩትን የአብሮነት እሴት በማጎልበት ለሰላም ሊተጉ እንደሚገባ ተመላከተ

 

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ጠብቀው ያቆዩትን የመደጋገፍና የአብሮነት እሴት በማጎልበት ለሰላም ሊተጉ እንደሚገባ የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።

የሀይማኖት አባቶቹ የህብር ቀንን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ስራ አስኪያጅና የባህርዳር እና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ አብርሀም አዲሱ ዓመት ሁሉም ለሰላም በመቆም ፈጣሪ የሚወደውን ስራ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ለሰላም፣ ለአንድነትና ለአብሮነት እንዲሁም ለመደጋገፍ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ጠቁመው፤ አዲሱን ዓመት ስንቀበል በንሰሀ ያለፈውን ይቅር በማለት ለሚመጣውም የፈጣሪን ፈቃድ ለመፈጸም መነሳሳት አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ የሁላችንም ፍላጎት ሰላም፣ ደስታ፣ ፍቅርና አንድነት ነው ብለዋል።

የየትኛውም እምነት ተከታዮች ሰላምን ምርጫ በማድረግ ለሰላምና ለአብሮነት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባቸው አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን የጳጳሳት ጉባኤ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት የቤተሰብ፣ የምእመናንና የወጣቶች ሀዋሪያዊ አገልግሎት ዳይሬክተር አባ አብነት አበበ፤ በአዲሱ ዓመት ለሰላምና ለአንድነት በመትጋት ሁሉም የሚጠበቅበትን መወጣት እንዳለበት ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሕብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ የምንቀበለው ዓመት እርስ በርስ ተከባብረን ይቅር ተባብለን መሆን አለበት በማለት ገልጸው፤ ዓመቱ አንዱ ለአንዱ የፈውስ ምክንያት ሆኖ የሚኖርበት መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያን ካውንስል ዋና ጸሃፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ የምንቀበለው ዓመት ለሀገር እና ለህዝብ መልካም ነገር የምንሰራበት መሆን አለበት ብለዋል።

እንዲሁም ሀገራችንን የምናገለግልበትና እጅ ለእጅ ተያይዘን ለሰላም የምንቆምበት መሆን አለበት ሲሉም ተናግረዋል።

የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተክርስትያን ፕሬዚዳንት ፓስተር ታደሰ አዱኛ ያለፈውን በመተው ክፉ ሀሳብን በማስወገድ ራስን በማረቅ መልካምነትን መላበስ እንደሚገባ አመላክተው፤ ከጸሎት ባለፈ ፈጣሪ የሰጠንን ሰላም ጠብቀን ለትውልድ ማስተላለፍ አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተ-ክርስቲያን ዋና ጸሀፊ ዶክተር ስምኦን ሙላቱ፤ ለተጨመረልን ዓመት ፈጣሪን እያመሰገንን ክፋትና ተንኮልን ማስወገድ እንደሚገባ አመላክተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

በሚያልፍ ዘመን ክፋት ምቀኝነትን ሳይሆን ፈጣሪ የሚወደውን ተግባር እየፈጸምን ልንኖር ይገባል ሲሉም አክለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.