ዋልያዎቹ በ2025 የሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ 2ኛ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዋልያዎቹ በ2025 የሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ይገጥማሉ፡፡
ጨዋታው ምሽት 4 ሠዓት ላይ በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ቤንጃሚን ምካፓ ብሔራዊ ስታዲየም ይደረጋል።
ህመም እና ጉዳት ላይ የነበሩት አብነት ደምሴ እና ወገኔ ገዛኸኝም ዋልያዎቹ ትናንት በአደረጉት የመጨረሻ ልምምድ ላይ መገኘታቸውን የእግር ኳስ ፌደሬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
በዛሬው ጨዋታም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አረንጓዴ መለያ፣ ቢጫ ቁምጣ እና ቀይ ካሶተኒ የሚጠቀም ሲሆን÷ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተጫዋቾች ደግሞ ሰማያዊ መለያ የሚለብሱ ይሆናል።
አልጄሪያዊው ላሎህ ቤንራሃም (ዋና)፣ ቱኒዚያዊው አይመን ኢስማኤል (ረዳት)፣ ሊቢያዊው ዋሂድ አል ጃዋህ (ረዳት) እና አልጄሪያዊው ነቢል ቦውካሊፋ (4ኛ ዳኛ) ጨዋታውን እንደሚመሩት ተገልጿል፡፡
በ2025 የሞሮኮ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከታንዛኒያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ያለምንም ጎል በመለያየት ነጥብ መጋራቱ ይታወሳል፡፡