ኅብረ ብሔራዊነታችን መልካችን፣ አንድነታችን ደግሞ ህልውናችን ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኅብረ ብሔራዊነታችን መልካችን፣ አንድነታችን ደግሞ ህልውናችን ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ”ኅብር” ቀን በማስመልከት በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ኢትዮጵያ የብዙ ብሔሮች፣ የብዙ ቋንቋዎች፣ የብዙ ባህሎች፣ የብዙ እምነቶች፣ የብዙ ሥልጣኔዎች፣ የብዙ ጀግኖች፣ ሀገር ናት። ኢትዮጵያ ኅብር ናት ብለዋል።
ሁሉም የኛ በእኛ ለእኛ የተሰጡ ናቸው በማለት ገልጸው፤ ሁሉን እናከብራለን፤ በሁሉም እንኮራለን ሲሉ ገልፀዋል።
ኅብረ ብሔራዊነታችን መልካችን፣ አንድነታችን ደግሞ ህልውናችን ነው፤ እነዚህ ኅብራዊ ጸጋዎች በአንዲት ሀገር በኢትዮጵያ የሚገኙ ናቸው፤ ዓላማችን አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መገንባት ነው። ግባችን የኢትዮጵያ ብልጽግና ነው። ይህ ነው አንድነታችን ሲሉም ነው ያሰፈሩት።
የተበታተንን ኅብሮች አይደለንም፤ የተጨፈለቅን አንድ ዓይነቶችም አይደለንም። እኛ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ያለን ኢትዮጵያውያን ነን ብለዋል።