የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ከ500 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች ማዕድ አጋራ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ከ500 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች፣ የሀገር ባለውለታዎችና በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የመንግስት ሰራተኞች ማዕድ አጋርተዋል፡፡
ይህንን አስመልክቶ ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው÷የምናጋራው ማዕድ ብቻ ሳይሆን ለወገኖቻችን ያለንን ፍቅርና አክብሮትን ጭምር ሲሆን ማዕድ ማጋራቱ ወገኖቻችን በዓሉን በደስታ እንዲያከብሩት የሚረዳ ነው ብለዋል::
የመንግስትን የሰው ተኮር ፖሊሲ፣ አቅጣጫና ጥሪ በመቀበል ሰርተው ካገኙት ለወገኖቻቸው ማካፈልን ባሕል ላደረጉ የከተማዋ ባለሀብቶች እና በጎ ፈቃደኞች ለወገኖቻቸው ለሚያደርጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡