ለየትኛውም የውጪ ወረራ ያልተንበረከክነው በአንድነታችንና በጀግኖች አባቶች መስዋዕትነት ነው – አቶ ጥላሁን ከበደ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለየትኛውም የውጪ ወረራ ያልተንበረከክነው በኢትዮጵያውያን አንድነት እና በጀግኖች አባቶች መስዋዕትነት ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ፡፡
ጳጉሜን 3 የሉዓላዊነት ቀን “ኅብር ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት” በሚል መሪ ሃሳብ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እየተከበረ ነው፡
በአከባበሩ ላይ የተገኙት አቶ ጥላሁን÷ ለየትኛውም የውጪ ወረራ ያልተንበረከክነው በኢትዮጵያውያን አንድነት እና ጀግኖች አባቶች መስዋዕት ከፍለው ሀገር ማሻገር በመቻላቸው ነው ብለዋል።
ቀደምት አባቶቻችን በዘመናዊና በሰለጠነ የጦር ስልት ኢትዮጵያን ማንበርከክ አለብን ብለው የውስጥና የውጪ ባንዳዎችን ይዘው ሙከራ ቢያደርጉም በጀግኖች አርበኞች ድል መነሳታቸውን አውስተዋል።
ኢትዮጵያ የነፃነት ሳይሆን የድል ቀን የምታከብር ብቸኛ ሀገር መሆኗን ገልፀው÷ ዛሬም ኢትዮጵያን ለማንበርከክ እና ለማሳነስ የሚሰሩ ሃይሎችን ዋጋ ከፍለው ለመመለስ ዝግጁ ለሆኑት ሁሉንም የጸጥታ ሃይሎች አመስግነዋል፡፡
በአንድነት በመቆም፣ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው፣ በየተሰማራንበት ውጤታማና አርበኛ በመሆን ሁለንተናዊ ሉዓላዊነታችን እናረጋግጥ ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸውንም የርዕሰ መስተዳድሩ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡